በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተከፈተ የተባለው የተኩስ እሩምታ
ሰኞ፣ ኅዳር 30 2017ድንጋጤን የፈጠረው የከተሞች ውስጥ የተኩስ እሩምታ
ወደ ተሃድሶ መዕከላት እያመሩ ነበር በተባሉ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የከተማዋ አከባቢዎች ተከሰተ በተባለው የጦር መሳርያ ተኩስ እሩምታ በነዋሪዎች ዘንድ ድንጋጤን መፍጠሩ ተመለከተ፡፡ መሰል የተኩስ እሩምታዎች በአምቦ እና ሌሎችም ከተሞች በስፋት መሰማቱ በየከተሞቹ የሚገኙ ነዋሪዎች ዘንድ ድንጋጤ መፍጠሩ ተነግሯል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከአንድ ሳምንት በፊት በይፋ ያስታወቀውከታጣቂዎች ጋር ተደርሷል ያለው የሰላም ስምምነት ምንነትና ዳራው ለህዝብ በይፋ እንዲገለጽ ተጠይቋል፡፡
በትናንትናው እለት አዲስ አበባ ውስጥ በተሰማው የተኩስ እሩምታ መረበሻቸውን ገልጸው አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ ነዋሪ፤ በተለይም ከመገናኛ እስከ ጉርድ ሾላ አከባቢ ሳያቋርጥ የተሰማው የተኩስ እሩምታን ምንነት ያወቁት አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዩ ላይ መግለጫ ካወጣ በኋላ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እንደ ነዋሪው አስተያየት ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ከታጣቂዎች ጋር ተከናወነ የተባለውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በገፍ እየመጡ መሆኑን በመገናኛ ብዙሃን መመልታቸውን በአዎንታዊ መልኩ ብወደስም በታጣቂዎች አገባብና ክትትል ላይ ጠንካራ መርህ መከተል ያስፈልጋል፡፡ “ታጣቂዎቹ መግባታቸው እሰዮ ነው፡፡ የሆነውንም የሚጋትም ነው ብለን ብናልፈው ግን በከተማ መሃል ሲያልፉ ትንሽ ገለጻ ያስፈልግ ነበር፡፡ በከተማ መሃል መተኮስ ልክ አይደለም፡፡ እጀባ እና ጥንቃቄ የሚስፈልግ ሆኖ ሳለ ስንሽ በዚህ መልክ መሆኑ ሰውን ቅር አሰኝቶታል” ሲሉ ስሜታቸውን አጋርተውናል፡፡
ምንም እንኳ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም የታጣቂዎች ውጊያ አቋርጠው መግባትም የሚበረታታ ያሉት አስተያየት ሰጪው ሁኔቱ የሚያስተላልፈው አበረታች ያሉት መልእክትም “ስልጣን በምርጫ ብቻ ልተላለፍ እንደምችል ብያስረዳም ግን ደግሞ ሃሳብ ያለው ፖለቲካ ድርጅት እንደሚስፈልግ ያመላከተም ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ትናንት በተለያዩ የከተማዋ አከባቢዎች የተሰማው የጦር መሣሪያ ድምፅን ተከትሎ አመሻሹን ባወጣው ይፋዊ መግለጫ፤ የመንግስትን የሠላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ተሃድሶ ሥልጠና ማዕከላት በሚጓዙ የቀድሞ የኦነግ ታጣቂ ቡድን አባላት የተሰማውን የተኩስ ድምጽ ተከትሎ ለተፈጠረው የዜጎች መደናገጥና መረበሽ ይቅርታን ጠይቋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ በቀጣይ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ከፍተኛ ጥንቃቄና የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድም ፍንጭ ሰጥቷል። በትናንቱ የተኩስ እሩምታ የሰው ህይወት ላይ ጉዳት ደርሶ እንደሆን በዶይቼ ቬለ የተጠየቁት የአዲስ አበባ ፖሊስ ቃል አቀባይ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ግን ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጡም፡፡ “የሰው ህይወት ማለፍን በተመለከተ የደረሰኝ መረጃ ስለሌለ እሱን እናጣራለን” ብለዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ውጪም በተለያዩ የክልል ከተሞች በነዋሪዎች ዘንድ መሰል ድንጋጤዎችን የፈጠረ የተኩስ እሩምታዎች መሰማታቸው ተሰምቷል፡፡ የአምቦ ከተማ ነዋሪም ይህንኑን አረጋግጠውልናል፡፡ “ያው እዚህ የሆነው በጫካ የነበሩ ታጣቂዎች ስገቡ መኪና ውስጥ ሆነው ከባድ የተኩስ እሩምታ ሲያከታትሉ ነበር፡፡ በዚያው በጣም የተደናገጡ አንዳዶቹ አከባቢያቸውን ለቀው የሸሹም ነበር፡፡ በኋላ ግን ነገሩን ስያረጋግጡ ወጥተው እያየ ነበር ማህበረሰቡ፡፡ ያው ቤተሰብም አላቸው አብሮአደግ ጓደኞችም ስላላቸው ሰው ውጥቶ ስመለከታቸውም ስቀበሉዋቸውም ነበር፡፡ እነዚህ ታጣቂዎች በከተማ ውስጥ እንዳሻቸው ስንቀሳቀሱ ተመልክተናል፡፡
እያንዳንዱ ቡድን የሚመሯቸው ስላላቸው በዚያው መልክ ስገቡና ስወጡ ተመልክተናል፡፡ በእንዳንድ ከተሞች በሚተኮሱ የተኩስ እሩምታዎች የሰው ህይወት ስለመጥፋቱ ተሰምቷል፡፡ እዚህ አምቦ አቅራቢያ ላይ በምትገኝ ጉደር እንዲህ ያለ ነገር ተሰምቷል፡፡ ታጣቂዎቹ ከተማ ውስጥ ሞተር ሳይክሎች ላይ ሆነው ወደሰማይ በእሩምታ ስተኩሱ ግን በአይነ ተመልክቻለሁ፡፡ አሁን እኔን እንደግለሰብ ጨምሮ ማህበረሰቡ ጋር የሚስተዋለው ሁለት ስሜት ነው፡፡ ታጣቂዎቹ ለምን በከፊል ገቡ ሁሉም ለምን አልገባም ብለው የሚሰጉ እንዳሉ እነዚህም ስታገሉ የነበሩ ነውና እንኳንም ገቡ ብለው በደስታ የተቀበሉም አሉ” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ዛሬ ጠዋት ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ከባለፈው ሳምንት ኅዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ መንግሥት ሽብርተኛ ሲል ከፈረጀው "ኦነግ ሸኔ" ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የሰላም ስምምነት ማድረጉንና ታጣቂዎቹ ወደ ተሃድሶ ሥልጠና ማዕከላት እየገቡ እንደሆነ በተለያዩ ሚዲያዎች መገለጹን ጉዳዩ ለሰላም ሊሰጥ ከሚገባው ቅድሚያ አንጻር ይበል የሚያሰኝ መልካም ዜና ሆኖ ማግነቱን አስታውቋል፡፡ መንግስት ሰላም ለማውረድ የሚያደርገውን ጥረት በማጠናከር በአማራ ክልልና በቀሪው ኦሮሚያ ክልል ካሉ ታጣቂዎች ጋር ወደ ሰላም ሊወስደው የሚችለውን ሁሉ እንዲያመቻችም ጠይቋል፡፡
በዚህም ላይ ተጨማሪ ማብራሪያን የሰጡን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ሙሉዓለም ተገኝወርቅ “ልብ ሊባል የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ በትጥቅ ትግል የፖለቲካ ጥያቄዎችን ለመፍታት ጫካ ገብተው የነበሩ ኃይሎች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ሲደረግ የነበረው የሰላም ስምምነት ግልፅ ባለመሆኑ ምክንያት ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ባለመቻሉ፤ አሁንም በኦሮሚያ ክልል በሰላም ስምምነቱ መሠረት እየገቡ ካሉ ታጣቂ ኃይሎቹ ጋር ያለውን ስምምነት ቅርፅ እና ይዘት ለህዝብ ግልፅ እንዲደረግ ነው የጠየቅነው” ብለዋል፡፡
በተለያዩ ቦታዎች ታጣቂዎቹ ወደ ከተማ ሲገቡ የጥይት ተኩስ ማድረጋቸው ንፁሀን ዜጎች ላይ ከፍተኛ ስጋት እና የስነ ልቦና ጫና የሚያሳድር አግባብነት የሌለው ተግባር መሆኑ ታውቆ በሁሉም ቦታዎች ላይ እንዲቆም ሲልም ኢዜማ ጠይቋል፡፡
ከታጣቂዎቹ ጋር ስለተደረገው ስምምነትዝርዝር እና ተፈጥሯል በሚል ስለተነሳው ክፍተት ተጨማሪ መረጃወን ለመጠየቅ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ደጋግመን ብንደውልም ለዛሬ ምላሻቸውን ባለማግኘታችን አስተያየታቸው በዚህ ዘጋባ ማካተት አልተቻለም፡፡ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ከምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች በብዛት እየተመለሱ ነው የተባለው የታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ መንገድ የመመለስ ሂደቱ ግን በምዕራብ ኦሮሚያ ቀሌም ወለጋ ዞን እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች መቀጠሉንም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ስዘግቡ ታይቷል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ዮሃንስ ገብረግዚአብሔር