1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ውሎ

ዓርብ፣ የካቲት 29 2016

ሰሞኑን በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ ብርቱ ውጊያዎች ጋብ ማለታቸው ተገለጠ ። በባሕርዳር ከተማ ትናንት ምሽት ቦንብ ፈንድቶ የተኩስ ድምፅም ለተወሰኑ ደቂቃዎች ይሰማ እንደነበር ታውቋል ።

https://p.dw.com/p/4dJsP
Äthiopien | Bahir Dar | Hauptstadt der Provinz Amhara
ምስል Matyas/Pond5 Images/IMAGO

ባሕርዳር ትናንት ቦንብ ፈንድቶ ተኩስም ነበር

ሰሞኑን በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ ብርቱ ውጊያዎች ጋብ ማለታቸው ተገለጠ በባሕርዳር ከተማ ትናንት ምሽት ቦንብ ፈንድቶ የተኩስ ድምፅም ለተወሰኑ ደቂቃዎች ይሰማ እንደነበር ታውቋል ውጥረት ባየለባት የፈረስ ቤት ከተማ ነጋዴዎች ሱቆቻቸዉን እንዲከፍቱ የመከላከያ አባላት እያስገደዷቸዉ መሆናቸው እና  አልፎ ሰዎች እየከፈቱ መሆናቸውን የዐይን ምስክሮች ተናግረዋል በሰሜን ሸዋ ዞን የተፋላሚ ኃይላት ፍጥጫ ቢኖርም ውጊያው ጋብ ማለቱ ተገልጧል  

ውጊያ በምዕራብ ጎጃም 

ምዕራብ ጎጃም ዞን፤ ደጋ ዳሞት ወረዳ፤ ፈረስ ቤት ከተማ፦ ሰሞኑን እጅግ ተደጋጋሚ ውጊያ ሲደረግባቸው ከቆዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች  አንዷ ናት ። የከተማዋ  ነዋሪ የሆኑ አንድ የዐይን እማኝ፦ ካለፈው እሁድ ጀምሮ እስከ ረቡዕ ድረስ በከተማዋ እና በከተማዋ ዙሪያ እጅግ ብርቱ ውጊያ እንደነበር ተናግረዋል ። ትናንት እና ዛሬ ግን አንድም የተኩስ ድምፅ እንደማይሰማ ገልጠዋል ። 

«ከከተማው ውጭ ዙሪያውን፦ ከተማውን ይዞ ውጊያ ነበር ከተማው ውስጥ አልፎ አልፎ ነበር የሚተኮሰው ትናንትና እና ዛሬ ፀጥ ብሏል ተኩስ ነገር የለም »

በፈረስ ቤት ከተማ ውስጥ ማክሰኞ ዕለት ጠዋት የጀመረው ውጊያ ቀኑን ሙሉ እንደነበረም የዐይን እማኙ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ።  በነጋታው ረቡዕ ደግሞ ከከተማው ወጣ ብሎ  ዙሪያውን ውጊያ እንደነበር ተናግረዋል።  ከፈረስ ቤት 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ሐሙስ ገበያ በሚባለው አካባቢ ተጨማሪ የመከላከያ ኃይል መጣ መባሉን ተከትሎ በከባድ የጦር መሣሪያ ጭምር  ከፍተኛ ውጊያ እንደነበረም ተገልጧል ። ትናንትና እና ዛሬን ጨምሮ ግን በፈረስ ቤት ከተማ የተኩስ ድምፅ አይሰማም፤ ሆኖም ከፍተኛ ውጥረት እና ጭንቀት እንዳለ ነዋሪዎች ተናግረዋል ። 

«እስከ ትናንትና ዝግ ነበር ዛሬ አሁን የመከላከያ አባላት እየዞሩ ሱቅ ክፈቱ ይላሉ እና አልፎ አልፎ ሰዎች እየከፈቱ ነው ሰዎች በእርግጥ ያለው ነገር ውጥረቱ የጭንቀት ነው እና አልፎ አልፎ እንደዚህ የከፈቱ አሉ ።»

የባሕር ዳር ከተማ ከፊል ገጽታ
የባሕር ዳር ከተማ ከፊል ገጽታ ፤ ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

ፈረስ ቤት እንዴት ዋለች?

በፈረስ ቤት ከተማ ሰዎች ወደ ውጪ መውጣት የጀመሩት ትናንት እና ዛሬ በመሆኑም በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በውል ማወቅ አልተቻለም ።

ሌላ አንድ በሰሜን ሸዋ የሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂ እንደሆኑ ለዶይቸ ቬለ የገለጡ ሰው፦ባለፈዉ እሁድ ዕለት ከባድ ውጊያ እንደነበር ተናግረዋል ።

«እኛ ተዋግተን ወደ ኋላ ባሸገሸግን ሰአት ዝም ብለው የፋኖ ቤት የትኛው ነው እያሉ የፋኖን ቤት አንድ ሁለት ቤት አቃጠሉ እየመረጡ ከዚያ በተረፈ እኛ ግን ከታጠቀ ኃይል   ነው የምንታገለው ሲቪል እንዲሰቃይ ያደረግነው ምንም ነገር የለም »

ትናንት እና እንዲሁም ዛሬ ውጊያው ሸዋ ሮቢት፣ ምንጃር እና መራቢቴን ጨምሮ በሁሉም አካባቢ ጋብ ማለቱንም አክለዋል ። ማክሰኞ እለት የፋኖ ታጣቂዎች ደብረብርሃን ከተማ ገብተው እንደነበርም አስታዉቀዋል።

የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት
ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ለአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤትም ሆነ ሌሎች ባለሥልጣናት ያደረግነው የስልክ ጥሪ ምላሽ አላገኘም ።ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የክልሉ ባለሥልጣናት

በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕርዳር ትናንት ምሽት አንድ ሰአት አካባቢ ቦንብ ፈንድቶ የተኩስ ድምፅም  ከአምስት እስከ 7 ቂቃዎች ግድም ይሰማ እንደነበር የዐይን እማኞች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ።

ስለ አማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ከመንግሥት ባለሥልጣናት በኩል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር መንገሻ ፈንታው፤ ለአማራ ክልል የሰላም እና ደኅንነት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንዲሁም ለመአከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አባል ዶ/ር አህመዲን አህመድ ብንደውልም ስልካቸው አይነሳም ። የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ስልክ  ጥሪ አይቀበልም ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ