1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

በሱዳን የርስ በርስ ጦርነት የፈጠረው አስከፊ ርሀብ

ሰኞ፣ መጋቢት 30 2016

በሱዳን የቀድሞው ፕሬዝድንት ኦማር አልበሺር ታማኝ ጄነራሎች፤ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ አብደል ፋታህ አልቡርሀንና የፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት አዛዥ ሞሃመድ ሀምዳን ዳጋሎ መካከል ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው ቀናት ቀሩት።

https://p.dw.com/p/4eYUI
ፎቶ ከማኅደር፤ የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ኦምዱርማን
ጦርነቱ በሱዳን አንድ ዓመት ሊደፍን ነው። ፎቶ ከማኅደር፤ የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ኦምዱርማን ምስል ohamed Khidir/Xinhua/picture alliance

በሱዳን የርስ በርስ ጦርነት የፈጠረው አስከፊ ርሀብ

በዚህ የጦርነት ጊዜ ውስጥ ክወደመው መሠረተ ልማትና ከፈረሱት ተቋማት ውጭ  ከ14 ሺህ በላይ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል። ሰባት ሚሊዮን ወደጎረቤት አገሮች ተሰደዋል፤ 18 ሚሊዮን ደግሞ እዚያው ሱዳን ውስጥ ከቤት ንበረታቸው ተፈናቅለው በክፍተኛ ችግር ውስጥ ይገኛሉ። ጦርነቱ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚውን ማውደም ማስተጓጎል ብቻ ሳይሆን እርዳታም እንዳይደርስ በማድረጉ፤ የሱዳን ሕዝብ ለረሀብ ተጋልጦ በሞት አፋፍ ላይ ይገኛል። የመንግሥታቱ ድርጅትና ሌሎች የርዳታ ድርጅቶችም ትርጉም በሌለው ጦርነት ምክንያት በሱዳን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የረሀብ  እልቂት ተከስቷል በማለት ጥሪያቸውን እያሰሙ ነው።

 

ሱዳንን ለረሀብ ያጋለጠው ጦርነት ምክንያት

 

ባልተጠበቀ ሁኔታና በፍጥነት ሱዳንን ለጠቅላላ ውድመትና ህዝቧንም ለከፋ ችግርና ጠኔ የዳረገው የእርስ በርስ ጦርነት አምና በዚህ ወቅት ነበር ዋና ከተማ ካርቱምን ማዕክል አድርጎ የፈነዳው።የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጄኔራል ኦማር አልበሺር ታማኞች የነበሩት የሱዳን ጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል አል ቡርሀንና የፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት ዋና አዛኝ ጄነራል ሞሃመድ ዳጋሎ እ.ኤ.እ.  በ2019 አም የህዝብ ግፊትና ተቃውሞ አይሎባቸው የነበሩትን ፕሬዝዳንት አል በሺርን በማሰውገድ በኩል አብረው የሠሩ ቢሆንም፤ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ግን፤ በግል ሥልጣንን ጠቅልሎ ለማያዝ ካለ ፍላጎት የዘለለ ሊሆን ይችላል በማይባል ምክንያት የጀመሩት ጦርነት፤ ዛሬ መላ ሱዳንን አዳርሶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለረህብና ጠኔ በመዳረግ ሱዳንን በዓለማችን የሰዎች ስቃይና እልቂት ተጠቃሽ አድርጓታል።

በቂ ሽፋን ያላገኘው የሱዳን ጦርነትና ርሀብ

 

የሱዳን ጦርነት ባጭር ጊዜ ውስጥ በሰፊው በመሰራጨትና በርካታ ሚሊዮንችም በማፈናቀልና እንዲሰደዱ በማድረግ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሁኗል። ሆኖም ግን፤ ብዙ ሽፋን እንዳልተሰጠውና ጦርነቱን ለማስቆምም አቅሙና ችሎታው ካላቸው ወገኖች ብዙም ፍላጎት እንዳልታየ ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት። ሁለቱም ወገኖች ያለ ሌላ ሦስተኛ ወገን ድጋፍ ጦረነቱን ለማስጀመርም ሆነ ለማስቀጠል አይችሉም ነበር የሚሉት እነዚሁ ታዛቢዎች፤ የቅርብም ሆነ የሩቅ ግን አቅሙ ያላቸው መንግሥታት ይልቁንም ሁለቱንም ወይም ከሁለቱ አንዱን በመርዳት ለሱዳን መውደምና ለሱዳንውያን እልቂት አስተዋጾ አድርገዋል በማለት ይወቅሳሉ። እየወደመች ካለችው ሱዳንና በጦርነትና ርሀብ እያለቁ ካሉት ሱዳኖች ይልቅ፤ ለአውሮጳውያኑ ዋናው አሳስቢው ጉዳይ ርሀብ ጦርነቱን ሸሽተው ለስደት መንገድ የገቡት ሱዳናውያን ወደ አውሮጳ እንዳያመሩ መሆኑን የአውሮጳ ሕብረት በቅርቡ ለግብጽ የለገሰውን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብም ለአብነት ይጠቅሳሉ እነዚሁ ታዛቢዎች።

ፎቶ ከማኅደር፤ የሱዳን ተፈናቃዮች መጠለያ በገዳሪፍ
የሱዳን ጦርነት ባጭር ጊዜ ውስጥ በሰፊው በመሰራጨትና በርካታ ሚሊዮንችም በማፈናቀልና እንዲሰደዱ በማድረግ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሁኗል። ፎቶ ከማኅደር፤ የሱዳን ተፈናቃዮች መጠለያ በገዳሪፍምስል -/AFP/Getty Images

የመንግሥታቱ ድርጅትና የርዳታ ድርጅቶች ጥሪ

ያም ሆኖ ግን በተለይ የመንግሥታቱ ድርጅትና የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች የሱዳንተፋላሚ ወገኖች የፈጠሩትን ቀውስና ረህብ በማጋለጥ፤ ዓለም ችግሩን አውቆ ማድረግ የሚገባውን በወቅቱ እንዲያደርግ ከመጎትጎት አላረፉም። እርዳታ ለማድረስም ተፋላሚ ወገኖች ከሚፈጥሩት ችግር ባሻገር የገንዘብ እጥረትም እንዳለባቸው በመግለጽ ጩኸታቸውን እያሰሙ ነው። የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ተወካይ ወይዘሪት ኤዴም ዎሶርኑ በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት በሰጡት ገለጻ፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረስብ ለሱዳን በቂ ትኩረት አለመስጠቱን አንስተዋል፤ «ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተገቢውን ትኩረት ባላመስጠቱና በችሮታ ማነስ ምክንያት ለሱዳን ሰብአዊ እርዳታ በበቂ ሁኔታ ለማድረስ እልተቻለም» በማለት ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ሱዳንን የረሳ መሆኑን አሳውቀዋል።

እርሀብ እንደ ጦር መሳሪያ

የዶቼ ቬለ ዘጋቢዋ ጃኒፈር ሆሊስ የመንግሥታቱ ድርጅት የሕጻናት መርጃ ድርጅት የሱዳን ተወካይ የሆኑትን ማንደእፕ ኦብሬንን ዋቢ አድርጋ፤ 2.9 ሚሊዮን ሕጻናት በጠኔ ምክንያት በሞት አፋፍ ላይ መሆናቸውን ዘግባለች። በሚቀጥሉት ሳምንታትና ወራትም 222 ሺህ ሕጻናት ሊሞቱ እንደሚችሉ፤ 7,000 አራስ እናቶችም እንደዚሁ በሞት አፋፍ ላይ እንደሆኑና ሊሞቱም እንደሚችሉም ገልጻለች።

ይህ ሁሉ ችግር እያለና ህዝብ በገፍ በረሀብ እየሞተም ግን፤ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ሰብአዊ እርዳታ እንዳይገባና ለህዝቡ እንዳይደርስ ችግር እንደሚፈጥሩ ነው የዶቼቬሌዋ ጄኒፈር ዘገባ የሚያስረዳው። ጊጋ የተባለው የጀርመን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ተመራማሪ  ወይዘሪት ሃገሬ አሊ እንደተናገረችውና የዶቼቨለዋ ጋዜጠኛ እንደጠቀሰችው ከሆነ፤ ተፍላሚዎቹ ወገኖች እንደውም ርሀብን  እንደጦር መሳሪያ ነው የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው። በተለይ የጀነራል ዳጋሎ ሀይሎች የሱዳን የዳቦ ቅርጫት የሚባለውን አልጂዚራ ግዛት ሲቆጣጠሩ የታየው ይህ ነው። ታጣቂዎች እህል ማቃጠላቸውንና መዝረፋቸውን በተጨማሪም ገበሬዎችን ከነሱ ጎን እንዲሰለፉ የሚያስገድዱ መሆኑንና ይህም የግብርናውን ሥራ ፈጽሞ እንዳስተጓጎለውም ገልጻለች። እንደጄኔርፈር ዘገባ ከሆን፤ የዳጋሎ ወታደሮች ምርትን እያወደሙና እየዘረፉ ገበሬዎችንም እንዲዘምቱ እያስገደዱ የምርት እጥረት ሲፈጥሩ፤ የጂኔራል አልቡርሀን ሀይሎች ደግሞ ለተቸገረው ህዝብ እርዳታ እንዳይደርስ ያግዳሉ ወይም ያስተጓጉላሉ።

  የኢንተርኔት መዘጋት ርሀቡን እንዴት እንዳባባሰው

በጦርነቱ ምክንያት በሱዳን በተለይም ክፉኛ በተጎዱት አካባቢዎች የኢንተርኔት አለመኖርም የርሀቡን ሁኔታ እንዳባባሰው የጄኔፈር ዘገባ ያስረዳል። ህዝቡ ገንዘብ ከውጭ ሲላክለት የነበረውና የሚቀበለውም፤ የሚገበያየውም በሞባይል የገንዘብ ዝውውር ስርአት የነበር ቢሆንም አሁን ግን ይህም በመቋረጡ መላኪያም መቀበያም የለም፤ ግብይትም ቆሟል፤ በማለት ህዝቡ ያለበትን ሁኒታ ጄኔፈር በዘገበዋ ግልጽ አድርጋለች። ለህዝቡ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ወደ ጦርነት የገቡት የሱዳን ጀኔራሎች ክገደሉትና ካሰደዱት ህዝብ በተጨማሪ ገበሬው እንዳያርስና ምርቱን እንዳይሰብሰብ በማድረግ፣ ንግዱና የገንዘብ ዝውውሩ እንዲታውክና እንዲቋረጥ፤ ሰብአዊ እርዳታ እንዳይገባና ለተራበው ህዝብ እንዳይደርስ በማድረግ፤ በሱዳን ታይቶ የማይታወቅ ረህብ እንዲከሰትና የሱዳን ህዝብ ባሳዛኝ ሁኔታ በረሀብ ምክንያት በገፍ እንዲሞት እያደረጉ መሆኑ በግልጽ የሚታይ አሳዛኝ ክስተት ሁኗል።

ፎቶ ከማኅደር፤ የሱዳን ግጭት ጦርነት ያፈናቀላቸው
ለወትሮው ሌሎች ስደተኞችን ይቀበሉና ያስተናግዱ የነበሩ ሱዳናውያን ለስደትና ረሀብ መዳረጋቸው የብዙዎችን ስሜት ነክሯል። ፎቶ ከማኅደር፤ የሱዳን ግጭት ጦርነት ያፈናቀላቸው ምስል AP/picture alliance

በሱዳን የሆነውና የተክስተው የፈጠረው ስሜት

ሱዳን የስደተኞች መነሃሪያና መተላለፊያ በመሆን የምትታወቅ ሀገር ናት። በተለይ በዚያ የኖሩና ያለፉ ኢትዮጵያውያውንና ኤርትራውያን የሱዳንን ህዝብ ደግነት በማውሳት ዛሬ በተፈጠረው ሁኔታ ከልብ እንደሚያዝኑ ነው ሲናገሩ የሚሰሙት። ሱዳን በስደትና በሥራ ለዓመታት የቆየውና  ዛሬ በኖርዌይ የአንድ በስደተኖች ላይ የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባልደረባ የሆነው ሙሀምድ ብርሀን ሙሃመድ ኑር በሱዳን እየደረሰ ባለው ሁኔታ በጣም ያዘነና ለሱዳን ህዝብ የሚገባው እንዳልሆነ ለዶቼ ቬለ በስልክ የገለጸው በጥልቅ የሀዘን ስሜት ነበር።

 

የሱዳኑ እርሀብ አስክፊነትና ልዩነት

በአሜሪካ የቱፍትስ ዩንቨርሲቲ የሰላም ድርጅት ዳይሬክተር፤ የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪና «የብዙሃን ርሀብ ትናንት እና ነገ» (Mass starvation:The History and Future of Famine) በሚል ረዕስ የተጻፈውን ጨምሮ በርካታ መጻሕፍትን የጻፉት አሌክስ ዴ ዋልም የዘንድሮው የሱዳን ረሀብ የተለየና የከፋ የሆነባቸውን ሦስት ምክንያቶችን፤ «አንደኛ ከዚህ ቀደም ከነበረው ድርቅና ርሀብ በተለየ ሁኒታ አሁን የሱዳን ኢኮኖሚ ወድሟል፤የሱዳን ዳቦ ቅርጫትነትም ተረት ሁኗል። ሁለተኛ ችግሩ በሱዳን ብቻ አይደለም። በሁሉም ጎረቤት አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ የኢኮኖሚ ችግር አለ። ሦስተኛ ይህ ሁሉም ሆኖ፤ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብን ደንታ የሰጠው አይመስልም» በማለት ሁኔታው እልቂት እንዳይስከትል የሚያሰጋ መሆኑን በመዘርዘር ገልጸዋል።

ምን መደረግ አለበት?

ሚስተር ዴዋል ይህን የሱዳንን የረሀብ እልቂት ለመግታት፤ ተፍላሚ ወገኖች ባስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስና እያደረሱት ያለውን እልቂትና ውድመት እንዲያቆሙ ማድረግ ዋናውና ቀዳሚዊው ተግባር መሆን ይኖርበታል ባይ ናቸው። ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብም የርዳታ ሰጭ ድርጅቶችን በበቂ የርዳታ ገንዘብ ማገዝ እንዳለበት ያሳስባሉ። ማሳሰቢያውን ሰምቶና ተቀብሎ ተግባራዊ የሚያደርግ ስለመኖሩ ግን ብዙዎች ይጠራጠራሉ። በዚህም ምክንያት የሱዳን ውድመትና የህዝቦቿ እልቂት የዘመናችን አሳዛኝ ክስተት እንዳይሆን ያሰጋል ነው የሚባለው።

ገበያው ንጉሤ

ሸዋዬ ለገሠ