የታኅሣሥ 28 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 28 2017ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደተለመደው በሳምንቱ መጨረሺያ ላይ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ድል ተቀዳጅተዋል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በደረጃ ሰንጠረዡ ቁልቁል ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ የምንጊዜም ተቀናቃኙ ሊቨርፑል ላይ ትናንት በርትቶ ታይቷል ። አርሰናል ከመሪው ሊቨርፑል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ የሚችልበትን አጋጣሚ ቅዳሜ ዕለት አምክኗል ። ማንቸስተር ሲቲ ተጋጣሚውን በሰፋ የግብ ልዩነት ሲረታ ቸልሲ ነጥብ ጥሏል ። ለገና ሰሞን እና ለአዲስ ዓመት ረፍት ላይ የነበረው የጀርመን ቡንደስሊጋ የፊታችን አርብ በዶርትሙንድ እና ባዬርን ሌቨርኩሰን ጨዋታ ዳግም ይጀምራል ።
አትሌቲክስ
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ቻይና ውስጥ በተካሄደ የማራቶን ሩጫ ፉክክር የቦታውን ክብረ ወሰን በመስበር ጭምር በማሸነፍ፥ በአጠቃላይ ውድድሩ ገንነው ወጥተዋል ። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሩቲ አጋ እና የሀገሯ ልጅ አትሌት ዳዊት ወልዴ ቻይና ውስጥ ትናንት በተኪያሄደው የዢያሜን የማራቶን ውድድር አሸናፊ ሆነዋል ።
በሺያመን ማራቶን የሴቶች ፉክክር አትሌት ሩቲ አጋ ውድድሩን ያሸነፈችው 2፡18፡46 በመሮጥ ሲሆን፥ ፈጣኑ የቦታው ሰዓት ተብሎም ተመዝግቦላታል ። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያቱ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ለማንም አላስደፈሩም ። 2:23:11 በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃ ያገኘችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጉተሚ ሾኔ ናት ። አትሌት ፍቅርተ ወረታ በበኩሏ ከጉተሚ 14 ሰከንዶች ብቻ በመዘግየት የሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች ። አራተኛ የወጣችው የኬንያዋ ሯጭ ሜርሲ ጄርፖን በመከተል አምስተኛ ደረጃም ያገኘችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ማሬ ዲባ (2:27:49) ናት ።
በወንዶች ተመሳሳይ የማራቶን ሩጫ ውድድር ደግሞ፦ ኢትዮጵያዊው አትሌት ዳዊት ወልዴ 2:06:06 የሆነ የቦታውን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ አሸንፏል ። ኢትዮጵያዊው አትሌት አሰፋ ቦኪ በበኩሉ የሌሶቶውን ሯጭ ተከትሎ ውድድሩን በ2፡06፡32 በማጠናቀቅ 3ኛ ደረጃን ይዟል ። ሁለተኛ ደረጃ ያገኘው ሌሶቶዋዊው አትሌት ቴቤሎ ራማኮንጎና አሰፋን የቀደመው ለጥቂት በ14 ሰከንዶች ነው ። በዚህ ፉክክር ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ጫሉ ደሶ (2:06:45)አራተኛ ደረጃ ሲያገኝ፤ የኤርትራው ሯጭ አቤሎም ከሠተ የአምስተኛ ደረጃ (2:07:05)አግኝቶ አጠናቋል ።
ከዚሁ ከአትሌቲክስ ዜና ሳንወጣ፦ ስፔን ውስጥ ትናንት በተከናወነው የኤልጎይባር አገር አቋራጭ ውድድርም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል ። በወንዶች የ10 ሺህ ሜትር ብርቱ ውድድር አትሌት በሪሁ አረጋዊ 29 ደቂቃ ከ36 ሰከንድ በመሮጥ በአንደኛነት አሸናፊ ሁኗል ። የቡሩንዲው ሯጭ ሮድሪጎ ክዊዜራ ከበሪሁ ለጥቂት በአንድ ሰከንድ ተቀድሞ ሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሳሙኤል ፍሬው 29 ደቂቃ ከ59 ሰከንድ በመሮጥ 3ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል ። የታኅሣሥ 7 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ኬኒያዊቷ አትሌት ቤአትሪስ ቼቤት ባሸነፈችበት የሴቶች 5 ሺህ ሜትር ፉክክር ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መልክናት ውዱ የሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ውድድሯን ያጠናቀቀችበት ጊዜም 26ደቂቃ ከ31 ሰከንድ ሁኖ ተመዝግቧል ። የቡሩንዲዋ አትሌት ፍራንሲን ኒዮሙኩንዚ መልክናትን በሁለት ሰከንድ ተከትላ ሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች ።
እግር ኳስ
በሳምንቱ መጨረሻ በተከናወኑ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች፦ ቸልሲ፤ አርሰናል፤ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ሊቨርፑል ነጥብ ጥለዋል ። ማንቸስተር ሲቲ በአንጻሩ ተጋጣሚው ዌስትሀም ዩናይትድን 4 ለ1 ጉድ አድርጓል ። እስካሁን 20 ጨዋታዎችን ያከናወነው ማንቸስተር ሲቲ በ34 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ በሚቀረው በመሪው ሊቨርፑልም በ12 ነጥብ ይበለጣል ።
ትናንት በሜዳው አንፊልድ ማንቸስተር ዩናይትድን ያስተናገደው ሊቨርፑል የማታ ማታ ከሽንፈት ተርፎ ሁለት እኩል በመለያየት ነጥብ ተጋርቷል ። በርካታ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን ያመከነው ሊቨርፑል ከአንድ ለዜሮ መመራት ተነስቶ ነው አቻ የወጣው ። ለማንቸስተር ዩናይትድ ቀዳሚዋን ግብ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ በ52ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል ። ለሊቨርፑል አቻ የምታደርገውን ግብ ደግሞ ኮዲ ጋክፖ በሰባት ደቂቃ ልዩነት ከመረብ አሳርፏል ። ሊቨርፑልን 2 ለ1 መሪ አድርጎ የነበረውን ፍጹም ቅጣት ምት ሞሐመድ ሣላኅ በ70ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል ። 80ኛው ደቂቃ ላይ ግን ከአራት የሊቨርፑል ተጨዋቾች ቁጥጥር ውጪ የነበረው አማድ ዲያሎ ለማንቸስተር ዩናይትድ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው ሁለት እኩል ተጠናቅቋል ።
በዕለቱ የሊቨርፑል የኋላ ተመላላሹ አሌክሳንደር አርኖልድ ቀድሞ ከነበረው ብቃቱ እጅግ ባነሰ ሁኔታ ላይ ነበር ። ምናልባትም ሰሞኑን በበጋው ወራት ሊያስፈርመው ፍላጎት ባሳየው ሪያል ማድሪድ ላይ የትናንቱ ብቃቱ ተጽእኖ ሊፈጥር ይችላል እየተባለ ነው ። የቡድን አጋሩ ቪርጂል ቫንጃይክ ግን የትናንቱ የአሌክሳንደር አቋም የሪያል ማድሪድ ፍላጎት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚል እምነት እንደሌለው ተናግሯል ። የሊቨርፑል አሰልጣኝ አርኔ ስሎት በበኩላቸው ለአሌክሳንደር አርኖልድ ተከራክረዋል ።
የአሌክሳንደር አርኖልድ እጣ ፈንታ
በትናንቱ የአሌክሳንደር አጨዋወት የተነሳ 10 ሰዎች ቢጠየቁ ዘጠኙ ከሪያል ማድሪድ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ችግር ይፈጥራል ቢሉም እሳቸው ግን አይፈጥርም የሚሉ አንደኛው መሆናቸውን ተናግረዋል ። በቡድናቸው ውስጥ ዲዬጎ ጆታን የመሰለ የፖርቹጋል ምርጥ ተጨዋች ቢኖርም በፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ አለመሆኑን ግን ጠቅሰዋል ። በተቃራኒው የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ የሆኑት ብሩኖ ፈርናንዴሽን እና ዲዮጎ ዳሎት ለማንቸስተር ዩናይትድ ተሰልፈው መጫወታቸው አሌክሳንደር አርኖልድ ላይ ጫና መፍጠሩን ገልጠዋል ። «እነዚህ እጅግ ምርጥ ምርጥ የፖርቹጋል ተጨዋቾች» በተሰለፉበት ጨዋታ የነበረው የአሌክሳንደር ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ እንደሚገባ ጠቁመዋል ። የኅዳር 30 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባበትናንቱ ግጥሚያ፦ የማንቸስተር ዩናይትዱ ሐሪ ማጉዌር ግብ ሊሆን የሚችል ኳስ ደርሶት ከግቡ አግዳሚ በላይ ልኳታል ። ከዘጠኝ ዓመታት ወዲህም ማንቸስተር ዩናይትድ በሊቨርፑል ሜዳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማሸነፍ የነበረውን ዕድል በማጨንገፉ በርካታ ደጋፊዎች ንዴታቸውን ገልጠዋል ።
ከከብ ግብ አግቢዎች
ሞሐመድ ሣላኅ የትናንቱን በፍጹም ቅጣት ምት የተገኘውን ጨምሮ በፕሬሚየር ሊጉ ግቦቹን 18 አድርሷል ። በኮከብ ግብ አግቢነትም እየመራ ነው ። የማንቸስተር ሲቲው ኧርሊንግ ኦላንድ በ16 ግቦች ይከተለዋል ። ኧርሊንግ ኦላንድ ቅዳሜ ዕለት ዌስትሐም ዩናይትድን 4 ለ1 ሲያሸንፉ ሁለቱን ግቦች አስቆጥሯል ። የኒውካስሉ አሌክሳንደር ኢሳቅ በ13 ግቦች ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። አሌክሳንደር ኢሳቅ ቅዳሜ ቶትንሀምን 2 ለ1 የማሸነፊያዋን ግብ በ38ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል ።
ዛሬ ማታ ዉልቭስ እና በ37 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኖቲንግሀም ፎረስት ተስተካካይ 20ኛ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ ። ኖቲንግሀም ፎረስት የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ በነጥብ ከአርሰናል ጋር ይስተካከላል፤ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ከሚቀረው መሪው ሊቨርፑል ጋር ደግሞ የነጥብ ልዩነቱ ስድስት ይሆናል ።
40 ነጥብ ሰብስቦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ቅዳሜ ዕለት ከብራይተን ጋር አንድ እኩል በመለያየት ነጥብ ጥሏል ። ቸልሲም በበኩሉ ከክሪስታል ጋር አንድ እኩል በመለያየት ቅዳሜ ዕለት ነጥብ ጥሏል ። በ36 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ኒውካስል በ35 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። በርመስ ኤቨርተንን 1 ለ0፤ አስቶን ቪላ ላይስተር ሲቲን 2 ለ1 አሸንፈዋል ። ፉልሀም እና ኢፕስዊች ታውን ትናንት ሁለት እኩል ተለያይተዋል ። ከትናንት በስትያ ብሬንትፎርድ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ በ6 ነጥብ የተወሰነው ሳውዝሐምፕተንን 5 ለ0 አደባይቷል ። ላይስተር ሲቲ እና ኢፕስዊች ታወን በ14 እና 16 ነጥብ ወራጅ ቀጣናው ውስጥ ይገኛሉ ። የኅዳር 23 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ቡንደስሊጋ
የጀርመን ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ፉክክር የፊታችን ዐርብ ዳግም ይጀምራል ። በጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ለሚያሰሉ በነበረው የገና በዓል እና የአዲስ ዓመት ወቅት ፋታ አግኝቶ የነበረው የቡንደስሊጋ ዐርብ የሚጀምረው በቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ባዬርን ሌቨርኩሰን መካከል በሚደረገው ግጥሚያ ነው ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ያለፈውን ዓመት የተሰናበተው በቮልፍስቡርግ ሜዳ በፎልክስ ቫገን አሬና ስታዲየም የ3 ለ1 ሽንፈትን በማስተናገድ ነበር ። በተቃራኒው ባዬርን ሌቨርኩሰን ተጋጣሚው ፍራይቡርግን 5 ለ1 አንኮታኩቶ ነው ወደ ጎርጎሪዮሱ 2025 የተሻገረው ። በቡንደስሊጋው ባዬርን ሌቨርኩሰን ከመሪው ባዬርን ሙይንሽን በአራት ነጥብ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። 25 ነጥብ ሰብስቦ በደረጃ ሰንጠረዡ ስድስተኛ ላይ የሚገኘው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከመሪው ባዬርን ሙይንሽን በ11 ነጥብ ይበለጣል ።
በደል በጀርመን የሴቶች ጂምናስቲክ
ጀርመን ውስጥ በሴቶች ጂምናስቲክ ስፖርት ብርቱ በደል እየደረሰ ነው የሚለው ዜና የሰሞኑ መነጋገሪያ ሁኗል ። በተለይ የቀድሞ የጀርመን ጂምናስቲክ ስፖርተኛ የነበረችው አትሌት ታቤያ አልት በኢንስታግራም ገጿ በአሰልጣኞች ይደርሳል ያለችውን በደል በአዲስ ዓመት መባቻ ዘርዝራ ጽፋለች ።
የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤቷ ታቤያ፦ «በደሉ የአንድ ጊዜ ክስተት ብቻ አይደለም»ም ብላለች ። «የምግብ መዛባት፤ የቅጣት ስልጠና፤ የሕመም ማስታገሻ ኪኒን፤ ዛቻ እና ማዋረድ የየዕለቱ ክስተት ነበር» ስትል በደሏን ዘርዝራ ጽፋለች ። ሽቱትጋርት ውስጥ በሚገኘው የጀርመን የሴቶች ጂምናስቲክ ማዕከል ውስጥ በነበረችባቸው በነዚያ ዓመታት ውስጥም፦ «ጤንነቴ ሆን ተብሎ እንዲያሽቆለቁል ተደርጓል» ስትልም በጽሑፏ ከሳለች ።
የ24 ዓመቷ የቀድሞ የጀርመን የሴቶች ጅምናስቲክ የኅዳር 23 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባቡድን አባል በአሰልጣኞች ሆን ተብሎ ይደርሳል ያለችውን በደል በማኅበራዊ መገናኛ አውታር ይፋ ያደረገችው የጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት መባቻ ሦስት ቀናት ቀደም ብሎ ነበር ።
የጀርመን ጂምናስቲክ ፌዴሬሽን ምላሽ
የየጀርመን ጂምናስቲክ ፌዴሬሽን በበኩሉ አትሌቷ ከአራት ዓመታት በፊት ያቀረበችውን አቤቱታ ችላ ብሏል መባሉን አስተባብሏል ። እንደውም ከሌሎች ጉዳዮች በተጨማሪ አትሌቷ ሽቱትጋርት ውስጥ ከሚገኙ የስፖርት ሳይኮሎጂስቶች ጋር እንድትነጋገር አመቻችተናል ብሏል ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለት የጂምናስቲክ አሰልጣኞች እስከ ፊታችን እሁድ ሳምንት ድረስ በሥራ ገበታቸው ላይ እንዳይገኙ መደረጋቸው ተዘግቧል ። ሌሎች የጂምናስቲክ አትሌቶች መሰል በደል አትሌቶች ላይ የሚደርስ ከሆነ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል ።
መሰል በደል በጀርመን የሴቶች ጂምናስቲክ ቡድን አባላት ላይ መድረሱ ከዚህ በፊትም ተዝግቦ ያውቃል ። ከአምስት ዓመት በፊት ኬሚንትስ ውስጥ በሚገነው የጂምናስቲክ ማዕከል አትሌቶች በአሰልጣኛቸው ጋብሪዬሌ ፍሬሼ ብርቱ በደል ይደርስባቸው እንደነበር ይፋ አድርገው ነበር ። አሰልጣኟ የጂምናስቲክ አትሌቶች ላይ «የስነልቦና ነውጥ» ፈጥረው እንደነበር በተደረገባቸው ምርመራ ይፋ መሆኑ ፌዴሬሽኑም በይፋ ይቅርታ ጠይቆ እንደነበር ይታወሳል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ