1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኑርንበርጉ ነዋሪ የኤሌክትሪካል ኢንጅነር ሳምሶን በቀለ ስኬት

ኂሩት መለሰ
ረቡዕ፣ ጥር 7 2017

የውጭ ዜጎች እድሉን ካገኙና ከተጣጣሩ በጀርመን ስኬታማ መሆን መቻላቸው ማሳያ የሆኑት አቶ ሳምሶን በአሁኑ ጊዜ ስደተኞች በምርጫ ዘመቻ ወቅት ስማቸው መጉደፉና ስብእናቸውም ዝቅ ተድርጎ መቅረቡ በጣም ይሰማቸዋል።ስደተኛን የሚጠሉት ቀኝ አክራሪዎች ጀርመን ውስጥ እየተጠናከሩ መምጣታቸው ከሚያሳስባቸው አንዱ ኤሌክትሪካል ኢንጅነር ሳምሶን በቀለ ናቸው።

https://p.dw.com/p/4p8pN
Samson Bekele, ein äthiopischer Elektroingenieur in Nürnberg
ምስል privat

የኑርንበርጉ ነዋሪ ኤሌክትሪካል ኢንጅነር ሳምሶን በቀለ ስኬት

መጀመሪያ በስደት የመጡባት ደቡብ ጀርመን የምትገኘው ኑርበርግ እስካሁን መኖሪያቸውና የሚሰሩባትም ከተማ ናት። እንግዳችን አቶ ሳምሶን በቀለ ኢትዮጵያ በፊዚክስ ትምህርት ጀምረው፣ ሩስያ በኋላም ኪቭ ዩክሬን ቀጥለው በመጨረሻም ኑርንበርግ ከፍጻሜ ያደረሱት የኤሌሌክትሪካል ምህንድስና ዛሬም የተሰማሩበት ሞያቸው ነው።  ምኞታቸው በነበረው በዚህ ሞያ ከመሰማራታቸው በፊት ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል። አዲስ አበባ የተወለዱትና ያደጉት የአንደኛ የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውንም በአዲስ አበባ ያጠናቀቁት ወጣቱ ሳምሶን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶስተኛ ዓመት የሚወዱት የፊዚክስ ተማሪ ላይ እያሉ ነበር ከሀገር ውጭ ለመማር የሞከሩት እርሳቸው እንዳሉት ወደዚህ ምርጫ የገቡት ትምህርቱን ከጨረሱ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያኔ በዚህ ትምሕርት ቢመረቁ ከአስተማሪነት ውጭ  መስራት በሚፈልጉባቸው ሌሎች የስራ መስኮች የመሰማራት እድላቸው ጠባብ ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ ከደረሱ በኋላ ነበር። 


ጥረታቸው ተሳክቶም ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ነጻ የትምሕርት እድል አግኝተው ከሄዱባት ከሩስያ ዋና ከተማ ሞስኮ ራቅ ብላ በምትገኝ ከተማ ቋንቋ ከተማሩ በኋላ እንደምኞታቸው ከፍተኛ ትምሕርታቸውን በኪቭ ዩክሬን የመቀጠል እድል ቢያገኙም ብዙም ሳይቆዩ ትምሕርታቸውን አቋረጡ፤ ኪቭንም ለቀው ወጡ። ኢትዮጵያ ውስጥ የደርግ መንግሥት ወድቆ ኢህአዲግ ሥልጣን ሲይዝ ትምሕርታቸውን እንደነበረው መቀጠል መቻላቸው ያጠራጠራቸው አቶ ሳምሶንና ሌሎች ተማሪዎች ከኪቭ ወደ ጀርመን መጡ።
በሩስያ እንደርሳቸው አገላለጽ እንደ ንጉሥ ተከብረው የቆዩት እነ አቶ ሳምሶን ኑርንበርግ  ፈጽሞ ያላሰቡት ነበር የጠበቃቸው። ያኔ እርሳቸውን ጨምሮ ስድስት ኢትዮጵያውያን በነበራቸው ቅርበት መነጋገር መቻላቸው ከሌሎችም ጋር መቀራረባቸው ሊደርስባቸው ከሚችል የስነ ልቦና ችግር ጠብቆናል ይላሉ። የሄዱበት ወቅት በጀርመን ተገን ጠያቂዎች የስራ ፈቃድም ሆነ የመማር እድል አልነበራቸውም። የሚሰጣቸው የገንዘብ ድጎማም ሩስያ ይሰጣቸው ከነበረው ጋር ሲነጻጸር  አነስተኛ ነበር።

Samson Bekele, ein äthiopischer Elektroingenieur in Nürnberg
ኢንጅነር ሳምሶን ከልጃቸው ጋር ምስል privat

 የኮሮና ወረርሽኝ፣መልካም አጋጣሚ ለኑርንበርግ ትጉሃን

አቶ ሳምሶን በስደተኞች ካምፕ እያሉ  ከአሜሪካን በተልዕኮ ትምሕርት የተከታተሉት የኤሌክትሪካል ምህንድስና ትምሕርት ነው የስራ ፈቃድ ያስገኘላቸው ። ይህም በአንድ የኤሌክትሪክ ስራ በተሰማራ ድርጅት ውስጥ በረዳትነት ለመቀጠር አበቃቸው። ኑርንበርግ ከመጡ ከስድስት ዓመት በኋላም በመንግሥት ፈቃድ ለሁለት ዓመት በተለይ ኤሌክትሮኒክስ ላይ ያተኮረ እርሳቸው ትክክለኛ ያሉት የኤሌክትሪካል ምህንድስና የሙያ ስልጠና ለሁለት ዓመት የመከታተል እድል አገኙ። ትምህርታቸውን ሲጨርሱም ኑርንበርግ በሚገኘው ሞቶሮላ በሚባል የአሜሪካን ኩባንያ ውስጥ ተቀጠሩ። በተለያዩ ጊዜያት ኩባንያው ለሌሎች ድርጅቶች ቢሸጥም አቶ ሳምሶን አሁንም እዚያው ኩባንያ ውስጥ በሙያቸው መስራታቸውን ቀጥለዋል። 
አቶ ሳምሶን ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ናቸው። ትዳር የመሰረቱትም በተለይም በኑርንበርግ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ እያሉ እርዳታ በፈለጉበት ወቅት በፈቃደኝነት ካገዟቸው ጀርመናዊት ጋር ነው። በሚወዱት ሞያ በመሰማራታቸው በሙያቸውም ከብዙ ጀርመናውያን ጋር መተዋወቅ በመቻላቸው ደስተኛ ናቸው። አልፎ አልፎ ግን ባገኟቸው ቁጥር ማንነታቸውን እንደ አዲስ በሚጠይቋቸው ጀርመኖች ሁሌም መገረማቸው አልቀረም።

ኢንጅነር ሳምሶን በቀለ
ኢንጅነር ሳምሶን በቀለምስል privat

ስደተኞችን የሚረዳ የኢትዮጵያውያን ማህበር በኑርንበርግ 
የውጭ ዜጎች በጀርመን እድሉን ካገኙና ከተጣጣሩ በጀርመን ስኬታማ መሆን መቻላቸው ማሳያ የሆኑት አቶ ሳምሶን በአሁኑ ጊዜ ስደተኞች በምርጫ ዘመቻ ወቅት ስማቸው ማጉደፍና ስብእናቸውን ዝቅ ተድርጎ መቅረቡ በጣም ይሰማቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ጀርመን ውስጥ ቀኝ አክራሪዎች እየተጠናከሩ መምጣታቸው የውጭ ዜጎችን ማሳሳቡ አልቀረም ቀኝ ጽንፈኛው አማራጭ ለጀርመን bn,ጀርመንኛ ምህጻሩ AFD የተባለው ፓርቲ በአሁኑ ጊዜ በህዝብ ድጋፍ ቀዳሚውን ቦታ መያዙ ከሚነገርለት ከክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ በጀርመንኛው ምኅህጻሩ ከCDU ቀጥሎ ያለውን ስፍራ መያዙ አሳስቧል ።ይህም ከ6 ሳምንት በሚካሄደው ወቅቱን ያልጠበቀ የጀርመን ምርጫ ውጤት ላይ  ሊኖር የሚችለው ተጽእኖ ማነጋገሩ አልቀረም። አቶ ሳምሶን በመጪው የጀርመን ምርጫ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ ያሸንፋል የሚል ተስፋ አላቸው። 
አቶ ሳምሶን አሁን ከኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ ስራቸው ጎን ለጎን የሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ትምሕርትም እየተከታተሉ ነው።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የባለቤታቸው ታናሽ ወንድም በዩጋንዳ  በሚያካሂደው ፕሮጀክት ውስጥ ለታቀፉ ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት ሙያዊ ስልጠና ይሰጣሉ። ከባለቤታቸው ጋርም አፍሪቃን የሚያስተዋውቁ ዝግጅቶችን በራድዮ ያስተላልፋሉ።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ