የአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት ምርጫ ውጤትና አንድምታው
ማክሰኞ፣ ሰኔ 4 2016በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የ27ቱ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ዜጎች ለአምስት ዓመታት የሚያገለግሉዋቸውን የህዝብ እንደራሴዎች ባለፈው ሳምንት መርጠዋል። ሐሙስ ተጀምሮ እሁድ ያበቃው የዚህ ምርጫ ውጤት ተጨማሪ መቀመጫዎችን ያገኙትን ቀኝ ጽንፈኞችንና ደጋፊዎቻቸውን ሲያስፈነድቅ ብዙ መቀመጫዎች የተወሰዱባቸውን ነባር ፓርቲዎችን ደግሞ አስደንግጧል። በፈረንሳይ «ራሰምብልሞ ናስዮናል» በምህጻሩ NR የተባለው ማሪን ለፔን የሚመሩት ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ማሸነፉ እንደታወቀ የፈረንሳዩን ፕሬዝዳንት ወዳልተጠበቀ እርምጃ ወስዷል። በምጫው ማሪን ለፔን የሚመሩት RN ከ31 በመቶ በላይ ድምጽ ሲያሸንፍ ለዘብተኛው የማክሮ ፓርቲ ረኔሶንስ በምህጻሩ RE ደግሞ ከ15 በመቶ ያነሰ ድምጽ በማግኘቱ ማክሮ የሀገሪቱን ምክር ቤት በትነው ከ20 ቀናት ባነሰ ጊዜ ምርጫ ለመጥራት ቀን ቆርጠው ወሰኑ።የቀኝ ጽንፈኛው «አማራጭ ለጀርመን» ፓርቲ መጠናከርና ስጋቱ
«በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 12 ላይ ከተመካከርኩ በኋላ የፓርላማችንን እጣ ፈንታ በምርጫ እንድትወስኑ እድሉን ልሰጣችሁ ወስኛለሁ።ስለዚህ ዛሬ ማታ ፓርላማውን እበትናለሁ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ምርጫው እንዲካሄድ የሚያስችለውን አዋጅ እፈርማለሁ። የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ሰኔ 30 ሁለተኛው ዙር ደግሞ ሐምሌ 7 2024 ዓም የሚካሄድ ይሆናል።»
የብሔረተኛ ፓርቲዎች ማንሰራራት ለፈረንሳይና ለአውሮጳ አደጋ ነው የሚሉት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ከትናንት በስተያ ምሽት ከኤሊዜ ቤተ መንግሥት ለህዝባቸው ባሰሙት ንግግር «ምንም እንዳልተፈጠረ ማስመሰል አልችልም ብለዋል። በዚህ ምርጫ ቀኝ ጽንፈኛው RN ያገኘው ድምጽ ከዛሬ አምስት ዓመቱ ምርጫ ውጤት በ10 በመቶ ከፍ ያለ ነው። የፓርቲው የቀድሞ መሪ ማሪን ለፔን የተገኘው ከፍተኛ ድምጽ ህዝቡ ባለፉት አራት አስርት ዓመታት ለየትኛውም ፓርቲ ያልሰጠው ድምጽ መሆኑን ይህም የህዝቡን ፍላጎት በግልጽ እንደሚያሳይ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።
«ክቡራትና ክቡራን!ውድ ጓዶች !ፈረንሳይ ተናግራለች። ይህ ታሪካዊ ምርጫ የሚያሳየው ህዝቡ ሲመርጥ ራሰምብልሞ ናስዮናል ከ32 በመቶ በላይ ድምጽ ማሸነፉን ነው። ይህ ህዝባዊ ኃይል በመላ ሀገሪቱ ሲያንሰራራ ለማየት ፈረንሳውያን ባለፉት 40 ዓመታት አንድም ፓርቲ ያላገኘውን ከፍተኛ ድምጽ ሰጥተውናል። » ከአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ ምርጫ ምን ይጠበቃል?
በጀርመን ትዩቢንገን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና መምህር ጋብርየል አቤልስ እንደሚሉት ምንም እንኳን ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎች አብልጫ ድምጽ እንደሚያሸንፉ ቢገመትም በፈረንሳይ የፕሬዝዳንቱ ፓርቲ አይሸነፉ ሽንፈት የገጠመው ህዝቡ እርግጠኛ ያልሆነባቸው ጉዳዮች በመኖራቸው ነው ይላሉ። ከዚህ ሌላ ለረኔሶንስ ሽንፈትን ለለፔን ፓርቲ ድልን ያጎናጸፈው ፓርቲያቸው RN የተከተለው ስልት ነው ብለዋል።
«አዎ በፈረንሳይ የፕሬዝዳንቱ ፓርቲ ያገኘው ድምጽ ከRN ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ያነሰ መሆኑ ፈጽሞ ያልተጠበቀ ነው። በፈረንሳይ ዋስትና ማጣት በጣም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ብሔራዊ ጉዳይ ነው።ከዚህ ሌላ ሌሎች ለውጦችም አሉ። የኤኮኖሚ ሁኔታዎችን የሚረዱበት መንገድ የቀጠለው የሽብር አደጋ፣የዩክሬን ጥያቄ እና ሌሎች ህዝቡ እርግጠኛ ያልሆነባቸው ጉዳዮች ላይ ማክሮ በተወሰነ ደረጃ ለመስራት ሞክረዋል። ሆኖም እነዚህን ችግሮች በሙሉ ማለፍ አልቻሉም። በአንጻሩ የማክሮንን ፓርቲ ለማስጠላት የራሰምብልሞ ወይም በተለይ የማሪ ለፔን ስልት ግን በጣም ስኬታማ ሆኗል።»
የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ ተንታኞችን ጠቅሶ እንደተናገረው ያለፈው ሳምንቱ የአውሮጳ ምርጫ ውጤት በአመዛኙ የተጠበቀው ቢሆንም ግን እንዳሰሰጋው አይደለም። ያም ሆኖም የፈረንሳይና የቤልጅየም የገዢው ፓርቲዎች ግን ክፉኛ ተጎድተዋል።የመሀል ቀኞቹና ግራዎቹ ደግሞ በአሁኑ ምርጫ ደኅና ቦታ ይዘዋል። ከምርጫው ውጤት በኋላ ፕሬዝዳንት ማክሮ የደረሱበት ፓርላማ በትኖ ምርጫ የመጥራት ውሳኔ ብዙዎችን አስገርሟል። ውሳኔያቸው የተለያዩ ግምቶችንም አሰንዝሯል። የአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤታዊ ምርጫ ዉጤት
ኮቪድ ያስከተለው የኤኮኖሚ ችግር የኑሮ ውድነት የዩክሬን ጦርነትና ሌሎች ፈተናዎችም ህዝቡ ነባሮቹን ፓርቲዎች እንዲሸሽ ለቀኝ ጽንፈኞች እንዲያደላ ምክንያት መሆናቸው ተደጋግሞ ሲነገር ቆይቷል። በጀርመንም የመራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የመሀል ግራው የሾሳል ዴሞክራቶቹ ፓርቲም እንደተጠበቀው ከቀኝ ጽንፈኛው «ከአማራጭ ለጀርመን» ፓርቲ ያነሰ 14 በመቶ ድምጽ ነው ያገኘው አማራጭ ለጀርመን በአሁኑ ምርጫ ያሸነፈው ድምጽ 15.9 በመቶ ነው ። ሾልዝ ቀኝ ጽንፈኞች በአሁኑ ምርጫ ስኬታማ መሆናቸውን አሳሳቢ ብለውታል። እርሳቸው በሚመሩት ጥምር መንግሥት ውስጥ የተካተቱትን የሌሎቹ ሁለት ፓርቲዎች ውጤትም መጥፎ ሲሉ ነው የገለጹት። እናም ከአሁን በኋላ እንደተለመደው መቀጠል አይቻልም ሲሉም አሳስበዋል። ይሁንና በጀርመን ያለው ሁኔታ ከፈረንሳይ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ነው ተባለው ። በሌላ በኩል ምርጫው ብዙ መቀመጫዎችን ያጡት አረንጓዴዎቹና የግራ ክንፍ ፓርቲዎች በስክንድኔቭያ ሀገራት አሸናፊ ሆነዋል።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ