«አማራ እና ትግራይ ክልሎች ተሳታፊ አልተለየም» ምክክር ኮሚሽን
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 12 2016
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ከአማራና ትግራይ ክልሎች በስተቀር በሌሎች ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የምክክር ተሳታፊዎችን እየለየ መሆኑን እስታወቀ።የኮሚሽኑ የመገናኛ ዘዴዎች ጉዳይ ኃላፊዎች እንደሚሉት በአማራ ክልል የሚደረገዉ ጦርነትና ትግራይ ክልል ከጦርነት በመውጣት ላይ ሂደት ላይ በመሆኑ ኃላፊዎቹ «የኮሚሽኑ ቁልፍ ተግባር« ያሉትን ተሳታፊዎችን መለየት አልቻሉም።ኮሚሽኑ በ5 ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በሚገኙ 700 ወረዳዎች ተሳታፊዎችን መለየቱን የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሠ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።ኮሚሽን በዚህ ዓመት ጥር ላይ ዋናውንየምክክር ጉባኤ ለማከናወን ጥረት እያደረገ መሆኑን ከዚህ በፊት አስታውቆ የነበረ ቢሆንም ሊሳካ አልቻለም።
የተሳታፊ ልየታ ሥራዎች ምን ደረጃ ላይ ደረሱ ?
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሚደረገው ውይይት ተሳታፊዎችን በመለየት ሂደት "እገዛ የሚያደርጉ ተባባሪ" ያላቸውን የሲቪክ ማህበራት ማዕቀፎችን ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ምክር ቤቶችን ፣ የመምህራን ማህበርን፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤን ፣ የዕድሮች ማህበራት ጥምረት እና የወረዳ አስተዳደሮችን ለይቶ እንቅስቃሴ ከጀመረ ቆይቷል። እስካሁን ይህ ተግባር በ700 ወረዳዎች መጠናቀቁን የገለፁት የኮሚሽኑ ዋና ቃል ዐቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሠ አማራ ክልል ጦርነት ውስጥ ፣ ትግራይ ክልል ከጦርነት የመውጣት ሂደት ላይ በመሆናቸው የልየታ ሥራው እየተከናወነባቸው አይደለም።
"አሁን በተጨባጭ የተሳታፊ ልየታ እያልተካሄደበት ያለው ነገር ግን ተሳታፊዎችን ለመለየት ቅድም ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ያሉባቸው ክልሎች ሁለት ብቻ ናቸው። አንደኛው የትግራይ ክልል ነው። ሌላኛው የአማራ ክልል ነው።"
በምክክሩ ትጥቅ ያነገቡ ወገኖች ዕጣ ምን ይሆን ?
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ነሐሴ 2 ቀን 2015 ዓ. ም አስቸኳይ በሚል አድርጎት በነበረው ሀገራዊ ጥሪ "በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች እየታዩ ያሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች የኮሚሽኑን ሥራ አዳጋች እያደረጉት ይገኛሉ" ብሎ ነበር። በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ኃይልን አማራጭ አድርገው ትጥቅ ያነገቡና ጫካ የገቡበት አጀንዳቸውን ይዘው ወደ ምክክር ይገባሉ የሚል ተስፋ ስለመኖሩ አቶ ጥበቡ ተናግረዋል።
እነዚህ ወገኖች ልዩነቶች፣ ሀሳቦች፣ አለመግባባቶች ስላሏቸው ያንን ምርጫ ማድረጋቸውን ገልፀው ፣ ጥያቄው ይህንን እንዴት በውይይት እንፍታ የሚለው መሆኑን ተናግረዋል። "አንፃራዊ የሆነ ሰላም ተገኝቶ በምክክር ሂደቱ አጀንዳቸውን ይዘው ወደ ምክክር ይገባሉ ብለን እናስባለን።"
በእስካሁኑ ሥራ የተቋሙ - ኮሚሽኑ ገለልተኝነት
የአጀንዳ ሀሳቦችን ማሰባሰብ የቀጣይ ሥራ ስለመሆኑ ተገልጿል። ኮሚሽኑ እስካሁን የቀረቡለት ጉልህ የአጀንዳ ሀሳቦችን መግለጽ ከቻለ ተጠይቆ ያንን ማድረግ የሥራውን ሂደት ይጎዳል በሚል ከመጥቀስ ተቆጥቧል።
የተሳታፊ ልየታ ሥራው ላይ ከመንግሥት ሊኖር ስለሚችል ጫና እና የተቋሙ ገልልተኝነት ለቀረበ ጥያቄ "ኮሚሽኑ ሥራውን የሚሠራው የመንግሥትን መዋቅር ተከትሎ አይደለም" ተብሏል። ለኮሚሽኑ የሚቀርብ የውጭ ድጋፍና ሊከተል ስለሚችል ተጽእኖን በሚመለከት ለቀረበ ጥያቄ በተሰጠ ምላሽ "ኮሚሽኑ የበጀት ችግር የለበትም" ሲሉ ኃላፊው መልሰዋል።
የሦስት ዓመታት የሥራ ዘመን በዐዋጅ የተሰጠው እና የካቲት 2014 ዓ.ም ሥራ የጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋናዉን ምክክር የሚጀምርበትን ጊዜ በተደጋጋሚ አራዝሟል። ኮሚሽኑ "እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ተፈጥሮ ማየት" የሚል ርዕይ አለው።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ