የኢትዮጵያና የጅቡቲ ግንኑኘት ያለበት ደረጃ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 6 2016ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ተማጋጋቢዎቹ ጎረቤት ሀገራት
ኢትዮጵያና ጅቡቲ ጠንካራ የኢኮኖሚ ፣ የፖለቲካና የፀጥታ ግንኙነት እንዳላቸዉ አንድ የጅቡቲ የምክር ቤት እንደራሴ አስታወቁ።ሁለቱ ሐገራት የአካባቢዉን ሠላምና ደሕንነት ለመጠበቅም አበክረዉ እንደሚጥሩ እንደራሴዉ አስታዉቀዋል።የኢትዮጵያ አብዛኛ የገቢና የወጪ ንግዷ የጅቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ ከሆነ ከ25 ዓመት በልጦታል።የዚያኑ ያክል ጅቡቲ ከአጠቃላይ የሐገር ውስጥ ምርቷ ግመሽ ያህሉን ለኢትዮጵያ ከምታከራየው ወደብ ታገኛለች።
ስለ ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ግንኙነት የፓርላማ አባሉ አስተያየት
ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር የመሆኗ ሀቅ እውን መሆኑን ተከትሎ የገቢ እንዲሁም የወጪ ንግዷ በጅቡቲ ወደብ ላይ የተመሠረተ ሆኗል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ አማራጭ የሚሰጥ የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመውም ይህንን ጫና ለማቃለል በሚል መሆኑን አስታውቋል። ጅቡቲ ውስጥ ከ አምስት ጊዜ በላይ የተመላለሰ መሆኑን የገለፀ አንድ ኢትዮጵያዊ ስለ ሁለቱ ሀገራት የተገነዘበውን አጋርቶናል።
ዶቼ ቬለ ጅቡቲ ከተማ ውስጥ ያገኛቸው አብዲ ኢሳ ቡላሌ የተባሉ አንድ የጅቡቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልየኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ግንኙነት ጠንካራ መሆኑንና ዘርፈ ብዙ በሆኑ ጉዳዮች በጎ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
"ግንኙነታችን ከዓመት ዓመት እያደገ ይገኛል። በአንድ ቀጣና ውስጥ በሰላም እየኖርን ነው ያለነው። እናም በኢኮኖሚ ፣ በፖለቲካ እና በሁሉም የደህንነት ጉዳዮች ጥሩ ግንኙነት አለን። አካባቢያችንን ለመጠበቅ የተቻለንን ሁሉ እየሰራን እንደሆነም ተስፋ እናደርጋለን።"
ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ምን ማለት ነች ?
ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የሰባት ሀገራት የጦር መንደሮች ማዕከል የሆነችው ጅቡቲ ከሳምንታት በፊት በሀገሪቱ የጣለው ከባድ ዝናብ የነዳጅ አጓጓዥ ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ገትቶች በኢትዮጵያ የነዳጅ ግብይት ላይ እጥረት ተከስቶ ነበር። ለመሆኑ ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ምን ማለት ነች? የሚለውን ከዚህ በፊት የጠየቅናቸው አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ሀገሪቱ የኢትዮጵያ ጉሮሮ መሆኗን ገልፀው ነበር።
"ኤርትራ ራሷን የቻለች ሀገር ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ጅቡቲ በኢትዮጵያ ዓይን ስትታይ ፋይዳዋ ጎልቶ የወጣ እንዲሆን ሆኗል" የሚሉት ስማቸውን ትተው ሀሳባቸውን የሚያጋሩን የዓለም አቀፍ ሕግና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ፤ ጅቡቲ በኢትዮጵያ የፀጥታ፣ የደኅንነት እንዲሁም የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖራት ተጽዕኖ እና ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑን ያስረዳሉ።ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ወደብ አልባ ትልቅ ሀገር የመሆኗን ያህል በየዓመቱ ከጎረቤቷ ጅቡቲ ለምታገኘው የወደብ አገልግሎት እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የተጠጋ ወጪ ታደርጋለች። ይህም የጅቡቲን ዓመታዊ ጠቅላላ ምርት ግማሽ ያህል ማለት ነው።
ሰለሞን ሙጪ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ