ዉይይት፣ የኦሮሚያና የአማራ ክልል ግጭቶች ለምን አይቆሙም?
እሑድ፣ መጋቢት 1 2016በዛሬዉ ዉይይታችን ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይ በኦሮሚያና አማራ ክልልሎች የሚደረገዉ ግጭት የሚያደርሰዉን ጥፋትና መፍትሔዉን በደምሳሳዉ እንቃኛለን።በልማዱ የትግራይ የሚባለዉ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም ድርድር ካበቃ ወዲሕ በኦሮሚያ ክልል የሚደረገዉን ግጭት ለማስቆም የተደረጉ ድርድሮችም ተመሳሳይ ዉጤት ያመጣሉ የሚል ተስፋ አሳድረዉ ነበር።
ይሁንና በመንግስትና መንግስት በአሸባሪነት በፈረጀዉ እራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሰ) ብሎ በሚጠራዉ ቡድን ተወካዮች መካከል ሁለቴ የተደረገዉ ድርድር ያለዉጤት አብቅቶ ዉጊያዉ አዲስ አበባ ጥግድ ድረስ እንደቀጠለ ነዉ።በአማራ ክልል ፋኖ በተባለዉ ቡድንና በመንግስት ፀጥታ ኃይላት መካከል ካለፈዉ ነሐሴ ጀምሮ የሚደረገዉ ዉጊያም የክልሉን ርዕሰ ከተማ ባሕርዳርን ጨምሮ ሰላም እንደነሳ ቀጥሏል።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድን ጨምሮ የፌደራሉ መንግስትና የገዢዉ ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከተለያዩ ክልሎች ባለስልጣናትና «የህዝብ ተወካይ» ከተባሉ ግለሰቦች ጋር ተወያይተዋል።ዉይይቱ በኢትዮጵያ ባጠቃላይ፣ በተለይ ደግሞ በኦሮሞያና በአማራ ክልሎች እየከፋ የመጣዉን ግጭትና ጥፋት በሰላም ለማስወገድ የሚረዳ ሁነኛ መፍትሔ ይጠቁማል የሚል ተስፋ አሳድሮ ነበር።
ይሁንና ብዙዎች እንዳሉት ዉይይቱ መፍትሔ ከመጠቆም ይልቅ ለመንግስትና ለባለስልጣናቱ ድጋፍ፣ አድናቆትና ዉዳሴ በመስጠት ተጠናቅቋል።
የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች፣የመብት ተሟጋቾች፣የርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ከሁሉም በላይ የየአካባቢዉ ነዋሪዎች እንደሚሉት በየግጭት፣ ዉጊያ ጥቃቶቹ የሚያልቅ፣ የሚቆስል፣የሚፈናቀለዉ ሕዝብና የምትደፈረዉ ሴት ቁጥር እየጨመረ ነዉ።የዓይን ምስክሮች እንዳሉት ተፋላሚ ኃይላት አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ጋር በሚገጥሙት ዉጊያ ከሚጎዳዉ ሰዉ በተጨማሪ የዚሕ ወይም የዚያኛዉ ወገን ደጋፊነሕ እያሉ የሚገድሉ፣የሚያግቱ፣ የሚዘርፉና የሚያንገላቱት ሰዉ ቁጥር ብዙ ነዉ።
አካባቢዎቹ በወታደራዊ ዕዝ (ኮማንድ ፖስት) የሚተዳደሩ በመሆናቸዉ የፍትሕ ወይም ያስተዳደር ጥያቄ ማንሳት አይቻልም።የመሰረታዊ አገልሎች ዝዉዉር ቆሟል ወይም በጣም ትንሽ ነዉ። መንገዶች ተዘግተዋል።የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦት ተቋርጧል።ሆስፒታሎች፣ የትምሕርት ተቋማት፣ሌላዉ ቀርቶ ወፍጮ ቤቶችና መደብሮች በሚፈለገዉ መጠን አይሰሩም።የመብራትና የዉኃ አገልግሎቶች በየጊዜዉ ይቆራረጣል።ኢንተርኔት በአብዛኛዉ አካባቢ የለም።ገበሬዉ ማምረት፣ ነጋዴዉ መዘዋወር ተስኖታል።
በህዝብ ላይ እስካሁን ከደረሰና ከሚደርሰዉ ግፍና በደልበጣም የከፋዉ ግጭቱ እንዲቆም የሚሹ ወገኖች ጥያቄ፣ ጥሪና ጥረት በጣም አናሳ ወይም የግብር ይዉጣ የሚመሳል መሆኑ ነዉ።የግጭቱ ደረጃ፣የሚደረሰዉ ጥፋት አሳሳቢነትና መፍትሔዉ የዛሬዉ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ ሶስት እንግዶች አሉን።
ነጋሽ መሐመድ