ኖትር-ዳም፤ ከቃጠሎ እድሳት በኋለ የተከፈተዉ የአዉሮጳ ምልክት
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 4 2017ኖትር-ዳም፤ ከቃጠሎ እድሳት በኋለ የተከፈተዉ የአዉሮጳ ምልክት
«ኖትር-ዳም ቤተ-ክርስትያን በአማርኛ የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ- ክርስትያን ማለት ነዉ። «ኖተር ማለት የኛ ማለት ነዉ፤ ዳም ማለት እመቤታችን ማለት ነዉ። »
ባለፈዉ ሳምንት (06.12.2024) ከአምስት ዓመታት እድሳት በኃላ ዳግም በይፋ ስለተከፈተዉ ስለኖተር-ዳም ካቴድራል ማለት፤ የፓሪሷ የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ዳግም መከፈት ከተዘጋጀ ዘገባ የተቀነጨ ነበር።
ፓሪስ ላይ በመካከለኛዉ ዘመን በተሰራዉ እና ወደ 850 ዓመት የሆነዉ የቅድስት ድንግል ማርያም ኖትር ዳም፤ የዓለም የታሪክ የሥነ-ጥበብ የሃይማኖት ማኅደርቤተ-ክርስቲያን ኖትር-ዳም ካቴድራል ከቃጠሎ አደጋ አምስት ዓመት በኋላ ታድሶ ዳግም በሩን ለጎብኝዎች ከፍቷል። የዛሬ አምስት ዓመት ሚያዝያ 7 ቀን 2011ዓ.ም አመሻሽ ላይ የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ ለዘጠኝ ሰዓታት በእሳት ሲጋይ በተለይ የካቴድራሉ ጣርያ ሙሉ በሙሉ መጋየቱ ብዙ አዉሮጳዉያንን አሳዝኖ ነበር። የዓለም የታሪክ የሥነ-ጥበብ የሃይማኖት ማኅደር የሆነዉ ኖትር-ዳም ካቴድራል፤ በጎርጎረሳዉያኑ 1991 ዓ.ም በመንግስታቱ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም ዩኔስኮ፤ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ይታወቃል። ባለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ ከአምስት ዓመታት በኋላ ካቴድራሉ ታድሶ ዳግም በሩ በይፋ ሲከፈት፤ በፈረንሳይ ብሎም በዓለም ታዋቂ የተባሉ ሰዎች በሥነ-ስርዓቱ ላይ ታድመዋል ። ጉዳዩን ከስፍራዉ ላይ የተከታተለችዉ የፓሪስዋ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ ቅኝቷን አጋርታናለች።
የፓሪስ ብሎም የመላ ፈረንሳይ ነዋሪዎች፤ ይህን ክስተት ከልብ በመነጨ ደስታ ነዉ የተከታተሉት። አስተያየታቸዉን እንደሚከተለዉ አጋርተዉናል። «በቅርብ ርቀት ላይ ነዉ የምኖረዉ። ከወራቶች ጀምሮ የካሬድራሉ ገጽታ እየተቀየረ ሲመጣ እያየሁ ነበር። ካቴድራሉን መጎብኘት ይኖርብኛል።» «በአምስት ዓመታት ጊዜ ዉስጥ ካቴድራሉን ታድሶ ለእይታ ብቁ መሆኑ እጅግ የሚገርም ነዉ። ዛሬ በይፋ መከፈቱም ትልቅ ታሪካዊ ክስተት ነዉ። »
በጎርጎረሳዉያኑ 1163 ተጀምሮ በ 1345 ዓ.ም ግንባታዉ የተጠቃለለዉ በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ እንብርት ላይ የሚገኘዉ የፈረንሳዉያኑ የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ-ክርስትያን ኖትር-ዳም ካቴድራል የአንደኛ እና የሁለተኛ ዓለም ጦርነት ያላወደመዉ፤የሰዉ ልጆች ጥበብ እድገትን ፖለቲካና ማኅበራዊ ኑሮ ታሪክን የያዘ ህንጻ እንደሆን ይነገርለታል።
ፓሪስ ከተማን አየሁ ያለ፤ ይህን ካቴድራል የጎበኘ መሆን አለበት ሲሉ ፈረንሳዉያን ይናገራሉ። የፓሪስ ነዋሪዎችም ካለ ፓሪስዋ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ-ክርስትያን ወይም ካለ ኖትር-ዳም ካቴድራልን ፓሪስ ፓሪስ አለመሆንዋን ይገልፃሉ። ካቴድራልዋ የፈረንሳይን ብሎም የሰዉ ልጆች ጥበብን፤ እምነትን ሥነ-ጥበብ ታሪክን አቅፎ የያዘ ሲሉ ባጭሩ ይገልጿታል። የጀርመኑ ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር-ሽታትይን ማየር የዛሬ አምስት ዓመት ካቴድራሉ በእሳት አደጋ በከፊል በወደመ ወቅት «የአዉሮጳ መለያ» የሆነዉን ካቴድራል ለመጠገን የጀርመንና የመለዉ አዉሮጳ ሕዝብ ርዳታ እንዲሰጥ ሲሉ ጠይቀዉ ነበር። የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም በፓሪሱ ኖትር ዳም ቃጠሎ ጀርመናዉያን አዝነናል ሲሉ ተናግረዉ ነበር።
ባለፈዉ ሳምንት ካቴድራሉ በይፋ በሩን ሲከፍት በነበረዉ ሥነ-ስርዓት ላይ ከባለቤታቸዉ ጋር የተገኙት የጀርመኑ ርዕሰ ብሔር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር፤ ኖተር-ዳም ድንቅ የህንፃ ጥበብ ብቻ ሳይሆን የአውሮጳ መለያ ተምሳሌት ነው ሲሉ ገልፀዉታል። የካቴድራሉ እድሳት በፍጥነት መጠናቀቅ ለፕሬዚዳንት ማክሮ በስልጣን ዘመን አንድ ስኬት የተወሰደበት እንደሆን የፓሪስዋ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ ነግራናለች።
ከ 12 ኛዉ ክፍለዘመን ጀምሮ ፓሪስ ከተማ የቆመዉና ሰማይ ጠቀስ ህንጻ የተባለዉ ካቴድራል፤ በቁመት ወደ 100 ዓመት ከሆነዉ የፓሪሱ አይፍል ማማ ትንሽ አነስ ያለ ግን በፓሪስ ሁለተኛዉ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ እንደሆን ይነገርለታል። የፓሪስ ነዋሪ የሆኑት ኢትዮጵያዊትዋ ወ/ሮ ማርታ ቀደም ሲል እንደነገሩን፤ ኖትር-ዳም ቤተ-ክርስትያን በአማርኛ የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ- ክርስትያን ማለት ነዉ።
«ኖትር ማለት የኛ ማለት ነዉ፤ ዳም ማለት እመቤታችን ማለት ነዉ። ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን ማለት ነዉ። » ብለዉን ነበር። በፓሪስ ነዋሪ የሆነችዉ የዶቼ ቬለዋ ሃይማኖት ጥሩነህ ስለካቴድራሉ ጥንታዊነት ተርካልናለች።
የዛሬ አምስት ዓመት ኖትር ዳም ካቴድራል በእሳት በጋየበት ወቅት በፓሪስ ነዋሪ የሆኑት ኢትዮጵያዊት ወ/ሮ አልማዝ ቃጠሎዉ ፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን ዓለም ማዘኑን እንዲህ ነበር የነገሩን። ይኑን እና የፈጣሪ ስራ ነዉ ሲሉ ወይዘሮ አልማዝ፤ ከቃጠሎዉ በፊት ካቴድራሉን ለማደስ የእርዳታ ገንዘብ ተጠይቆ ብዙም አልተዋጣም ነበር ሲሉ ነበር የነገሩን ዛሬ ካቴድራሉ ታድሶ ለፀሎት ብሎም ለጎብኝዎች ክፍት ሆንዋል።
«ኖትር-ዳም የፈረንሳይን የክርስትና ሃይማኖት ታሪክ የሚሳይ ብቻ ሳይሆን የአዉሮጳ ቅርስም ነዉ። ለዚህም ነዉ ከጀርመን የባህል ሚኒስትር ጋር በመነጋገር በመልሶ ግንባታዉ ላይ ለመሳተፍና ባለሞያዎችን እና ልምዳችንን በመቀያየር ርዳታ ለመስጠት ዝግጁነታችንን የገለፅኩት። የባህል ሚኒስትሮቹ በኖተር ዳሙ ካቴድራል እድሳት ላይ ምልከታዎቻቸዉን ይለዋወጣሉ። በዚህም አለ በዝያ በፓሪስ በተከሰተዉ ነገር ጀርመናዉያን እጅግ አዝነናል»
የፓሪስዋ የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ-ክርስቲያን ማለት ኖተር-ዳም ላይ ቃጠሎ ሲነሳ የፓሪስ ነዋሪዎች አብዛኞች አልቅሰዋል፤ በየጎዳናዉ በመሰባሰብ ፀልየዋል፤ መዝሙር ዘምረዋል። በፓሪስየሚገኙ ሌሎች አብያተ ክርስትያናትም ደውል ሲያሰሙ ማምሸታቸዉ በቀጥታዉ ስርጭት ቴሌቭዥን ሲሰራጭ ነበር። ኖትር-ዳም በዓመት ከ 12 እስከ 13 ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚጎበኘዉ የዓለም ታሪካዊ የቱሪስት መስዕብም እንደሆነ ተመልክቶአል። ቤተ-ክርስትያኒቱ በተለይ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ላይ የተደረገዉ የእሾህ አክሊል የተቀመጠበት ነዉ በመባሉ በሃይማኖቱ ተከታዮች ይታወቃል። ቤተ-ክርስትያኒቱ በወር በገባ የመጀመርያ አርብ እለት እለት በሚደረግ ፀሎት ላይም ለምዕመናን የአክሊል እሾሁ ለእይታ ይቀርብ እንደነበር ተመልክቶአል። አንድ የፓሪስ ጋዜጣ የእሾህ አክሊሉ ከእሳት መጋየት ተርፎአል ሲሉ አስነብቦም ነበር። ወ/ሮ ማርታ በኖትር-ዳም ስለአለዉ የእሾህ አክሊል ይህን ነግረዉን ነበር።
« የሾህ አክሊሉ ወር በገባ የመጀመርያዉ አርብ ይታያል ። በሁዳዴ ጾምም አርብ አርብ ይወጣል። እምድር ቤት የቤተክርስትያኒቱ ሙዚየም ይገኛል እና እሳት የደረሰበት አይመስለኝም አብዛኛዉ እቃ ተርፎአል ነዉ የሚባለዉ።» የኖትር ዳም ቃጠሎ እድሳት ብሎም የምረቃዉ ሥነ-ስርዓት ፈረንሳዉያንን አንድ ያደረገበት ክስተት እንደነበር ብሎም የዓለም ፖለቲከኞች እንዲገኛኑ መድረክ የፈጠረበትም እንደነበር የፓሪስዋ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ ተናግራለች። ሃይማኖት የኖተርዳም በአደጋዉ ምክንያት ለአለፉት አምስት ዓመታት መዘጋት የፈረንሳይን ብሎም የፓሪስን የቱሪዝም ገቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰበት ይነገራል።
ታሪካዊዉ የፓሪስ ቤተ-ክርስትያን ዳግም ለማነፅ፤ በርካታ የዓለም መንግሥታት ድጋፍ ዝግጁነታቸዉን አሳይተዋል። የፈረንሳይ ቱጃሮች ፤ የፈረንሳዩ የነዳጅ ኩባንያ እንዲሁም የፈረንሳዩ የመዋቢያዎች አምራች ኩባንያ የእሳት ቃጠሎዉ እንደተናሳ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላሮች መስጠታቸዉ ተነግሯል። ከዚህ ሌላ ስማችን እንዳይነገርብን ብለዉ እንዲሁ በሚሊዮን የሚቆጠር ድጋፍ ያደረጉ ጥቂቶች አይደሉም። ታሪካዊዉ የፓሪስ ካቴድራል ኖትር ዳምን ስላጋየዉ ቃጠሎ እንዴትነት በዉል ግን አልተነገረም አይታወቅምም። ይሁን እንጂ፤ ካቴድራሉ ካለፈዉ ሳምንት መጠናቀቅያ ጀምሮ የፀሎት ሥነስርዓቱን ጀምሯል፤ ጎብኝዎችም ካቴድራሉን ለመጎብኘት እየተመዘገቡ፤ በሩን አልፎ ዘልቆ ለመግባትም ረጅም ሰልፍ ቆመዉ እየጠበቁ ነዉ።
ሙሉ ጥንቅሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን!
አዜብ ታደሰ / ሃይማኖት ጥሩነህ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር