የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ታኅሳስ 10 ቀን 2017 ዓ.ም.
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 10 2017በአማራ ክልል የእንቅስቃሴ ገደቦችና ተጽእኖአቸው
በአማራ ክልል በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በላይ የዘለቀው ውጊያ ከሚያስከትለው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት በተጨማሪ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ ቀውሱን ማባባሱን የክልሉ ነዋሪዎች ለዶቼቬለ ተናግረዋል።በመንግሥትም ሆነ በክልሉ በሚንቀሳቀሰው በፋኖ የሚጣሉ እነዚህ የመጓጓዣ ገደቦች የሚያደረሱት ጉዳት እንዴት እንደሚታይ በዚህ ሳምንት የፌስቡክ ተከታዮቹን ሃሳብ ጠይቆ ነበር ።
በዚህ ጥያቄ ላይ ሀሳባቸውን ካካፈሉት አንዱ ታሪኩ ስሜነህ በፌስቡክ የችግሩን መንስኤና መፍትሔ ያሉትን ሰንዝረዋል። «ተፋላሚዎቹ በክልሉ ያለውን የጸጥታ ችግር በንግግር ከመፍታት አሁንም ምርጫቸውን ጦርነት አድርገው ገፍተውበታል"ጦርነት እንኳን እንደ ኢትዮጵያ በድህነት አረንቋ ላለች ሀገር ይቅርና ለባለጸጋዎቹ ሀገራትም አልጠቀመም ። ጦርነት አውዳሚ ነው። በዚህ ዘመን ጦርነትን ማሰብ ኃላቀርነት ነው።» ካሉ በኋላ «በእኔ እምነት ከህወሓት ጋር ፕሪቶሪያ ላይ የተስማማው መንግስት ከፋኖ ጋርም እንዲስማማ እፈልጋለሁ። » ሲሉ ስሜነህ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል
የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ገደብ
ተመስገን አየነው አሰጌ በአጭሩ «የጦርነት ውጤቱ ውድመት እና ሞት ስለሆነ ሰላማዊ መንገድን ምርጫችን ብናደረግ»የሚል ምክር አስተላልፈዋል። አንዱዓለም ዘለቀም ተመሳሳይ ሀሳብ አቅርበዋል«ሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች ሀገርንና ህዝብ ግምት ውስጥ በማስገባት ልዩነታቸውን አጥብበው እኔ አሸንፋለሁ እኔ አሸናፊ ነኝ ከማለት ወጥተው ቢደራደሩ የተሻለና ብቸኛው አማራጭ ነው። በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል። ወርቅውሀ አበራ ደግሞ ።«የመንግስት ወታደሮች ለህዝብ ሲሉ ትግራይን ለቀው እንደወጡት ለምን አማራ ክልልን ለቀው ወጥተው ችግሩን በንግግር አይፈቱም ህዝብኮ እየተጎዳ ነው» ሲሉ ለመንግሥት ጥሪ አቅርበዋል
ኤፍሬም ህላዌ ደግሞ ተስፋ የቆረጡ ይመስላል። «ከሁለቱም አቅጣጫ የሚደረጉ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እና የውጊያ አውዶች በሰዉ ህይወት በንብረት በአጠቃላይ ፖለቲካው በማህበራዊው በኢኮኖሚው ላይ ማወዳደሪያ በማይገኝለት ደረጃ ከፍተኛ ውድመትና ኪሳራ እየደረሠ ነው።»ካሉ በኋላ ከሁለቱም ወገን ምንም መፍትሔ የለም። ህዝቡም ከሁለቱ ወገን ገለልተኛ ሆኖ በንብረትና በሠው ውድመትና ሞት ተላምዶት ዝም ብሏል መፍትሔ የለውም »ብለዋል
ሄለን ከበደ ደግሞ ምክር አላቸው«መንግስት ጠንከር ያለ የፖለቲካ ውይይት አድርጎ ያኮርፉት ኃይሎች ፍላጎት ምድነው ብሎ ጠይቆ ፍላጎት አሟልቶ ወድ ድርድር መግባት ሰላም ይሻላል ሃገር እና ህዝብ ከወደመ በኋላ ምን ይሰራል ?ኑ ወደሰላም እያሉ በቴለቪዥን መስኮት ብቅ ብሎ ከማለት ጠንከር ያለ ውይይት ማድርግ ነው»የሚል
ጦርነቱ ምንም አልገባን ሲሉ አስተያየታቸውን የጀመሩት ግዛቸው ከፍአለ ምክንያቱም በማለት ይቀጥላሉ፣ምክንያቱም መንግስትም ፋኖም የሚያሰቃየው ህዝቡን ነው ሁለቱም ለህዝብ ነፃነት ይሉናል ሁለቱም ግን ያሰቃዩናል ብለዋል።
መሀመድ አብደላ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ግጭት አባባሽ መስለው ለታዩዋቸው ጥያቄዎች አቅርበው የሚበጅ ያሉትን መፍትኄ ጠቁመዋል። ለመሆኑ በዘመቻ መልክ በፌስቡክ ሜዳ ወጥታችሁ ሳትተያዩ እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ የጦርነት ነጋሪት የምትደልቁ ወገኖች1፣ ለመሆኑ ጦርሜዳውን ተቀላቅላችኋልወይ? በመሬት ያለውን ሐቅ ታውቁታላችሁ ወይስ ቀቢፀ ተስፋ አስክሯችሁ ነው? ካሉ በኋላ ለሁሉም የሚበጀው «ንግግርና እርቅ ነውና ከጨኸት አቋም ወጥታችሁ ኑና እንመካከር እና ሰላምን እናበርታ!!! የሚያዋጣው ይህ ብቻ ነው ሲሉ መክረዋል።
በኦሮምያ ሰላም እንዴት ይምጣ ?
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በቅርቡ በሰኚ ከሚመራው የኦነግ ኦነሰ አመራሮች ጋር አደረኩት ባለው ስምምነት የታጠቁ የሰራዊቱ አባላት የተሃድሶ ስልጠና ወደሚካሄድባቸው ማዕከላት እየገቡ እንደሆነ ተገልጿል።ከዚያም ቀደም ሲል በኦሮሚያ ሰላም ለማስፈን በክልሉና በፌደራል መንግስት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎች ሲተላለፉ ነበር ። ራሱን ኦነግ ኦነሰ ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋርም በታንዛኒያና ዛንዚባር የሰላም ድርድሮች ተደርገው ነበር። ይሁንና አሁንም በክልሉ ግጭቶች እየቀጠሉ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ታዲያ «በኦሮሚያ ክልል ዘላቂ ሰላም እንዴት ይምጣ? የሚለው ያለፈው ሳምንት የእንወያይ ዝግጅታችን ትኩረት ነበር። ለዚህ የዶቼቬለ ጥያቄ ናንሱ ማሃፊ በፌስቡክ «ሰላም የሚመጣው ሰው መሆን ከጎሳ ፣ ከቋንቋ እና ከሐይማኖት በላይ ሲቀድም ብቻ ነው። አንድ ሰው በችሎታው ፣ በትምህርቱ እና በባህሪው እንጂ በነገዱ ፣ በቋንቋው እና በሃይማኖቱ ሊመዘን አይገባም። ሁሉም ሰው ሰውነቱን አስቀድሞ በአንዲት የኢትዮጵያዊ ዜግነት ዣንጥላ ስር መኖር ከቻለ ሰላም ይመጣል ብዬ አምናለሁ። » በማለት የርሳቸውን አመለካከት አጋርተዋል።
የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ፈጸምኩ ያለው የሰላም ስምምነት ዳራ
የእህታለም አስተያየት ደግሞ ከዚህ ይለያል ። መንፈሳዊ ነው። « መጀመርያ አምላካችንን ሰለበደልን ሃገርአቀፍ ንሰሃ ማድረግ ከዚያ በኋላ ድርድሩም ክርክሩም ጦርነቱም መልክ ይይዛል ሁሉም ነገር አሰቀድሞ የሚሰራው በመንፈሳዊው ዓለም መሆኑ የታወቀ ነው ለዚህም ነው"ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን"የምንለው ብለዋል።ጉዱ ካሳ ዘ እንጅባራ በሚል ሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አስተያየት«ኢትዮጵያ ሰላምሽ ይብዛ »ሲል ዲማ ጎንጄ በጣም አጭር እና ግልጽ ያሉትን መልስ ሰጥተዋል። «ያለምንም ጫና እና ግፊት የኦሮሚያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ በኦሮሚያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ፣ ያልታጠቁ፣ ሲቪክ ማህበራት፣የፖለቲካ ድርጅቶች ወይንም በሌላ አባባል የኦሮሚያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ በሙሉ በአንድ መቀመጫ ላይ ቁጭ ብለው በመነጋገር ብቻ እና ብቻ ነው መፍትሄ ሊመጣ የሚችለው። ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።
ኃይለኛው ቅዝቃዜ በደጋማዎቹ የኢትዮጵያ ከተሞች
አዲስ አበባን ጨምሮ በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች ሰሞኑን የተከሰተው ጠንከር ያለ ብርድ ከዚህ ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ እየተዳከመ እንደሚሄድ የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለዶቼቬለ አስታውቋል።
ለኃይለኛው ቅዝቃዜ ፣ ከሳይቤሪያ ተነስቶ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ደረቅና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ምክንያት መሆኑንም ተናግሯል። ትእግስት ሰሎሞን በፌስቡክ
«ተመስገን ነው የሚባለው በዚህ ድህነት እንደውጭ ሀገራት በረዶ ቢሆን እንዴት ልንሆን ነው አስቡት እስቲ ፣እኛ ሰዎች ለፈጣሪ አንመችም ሲዘንብ አቤት ዝናቡ ጸሃይ ሲሆን አቤት ጸሃዩ እንላለን እሱ የፈቀደው ይሁን ጎዳና ላይ ያሉት ምን ይበሉ እኛ ልብስ ደራርበን ቤት ውስጥ በምቾት ተኝተን አይ ሰው«ብለዋል ።
በኢትዮጵያ የተከሰተው ኃይለኛ ቅዝቃዜ መንስኤና ማብቂያው
ወይኔ መስፍን «አኛን ያስጨነቀን ብርዱን መቋቋም እንዳንችል ኑሮ አስወድደዉ በጥቅምት አንድ አጥነት ሳንበላ አቅመ ቢስ ያረጉንን ሰዎች ጉዳይ ነው ፤በማለት እግረመንገዳቸውን ብሶታቸውን አሰምተዋል። ሀጎስ መሐሪም «ብርዱና ቅዝቃዜው ይለመዳል የህዝብ ሞት ነው ያሳሰበን»ሲሉ ወንድማገኝ ይልማ መቼም ከሙቀት ብርዱ ይሻላል ሲሉ ራሳቸውንም ሌላውንም አጽናንተዋል።
ሰብለ መርሻ ግን «እኔስ ኑሮው ነው የቆጠቆጠኝ»በማለት ከብርዱ ይልቅ የበረታባቸውን አሳውቀዋል።
ኂሩትመለሰ
ሸዋዬ ለገሠ