ስደተኞችን ለመግታት የአውሮጳ ኅብረት 1,07 ቢሊዮን ዶላር ለሊባኖስ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 24 2016የአውሮጳ ኅብረት የሶሪያ ስደተኞች ወደ ኅብረቱ ሃገራት እንዳይገቡ በማድረግ ረገድ ሊባኖስ ለምታደርገው ትብብር የ1,07 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ቃል መግባቱ ዛሬ ተገለጠ ። የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኡርዙላ ፎን ደር ላየን ከሊባኖስ ጠቅላይ ሚንስትር ናጂብ ሚካቲ ጋ ዛሬ ተነጋግረዋል ። ሊባኖስ መዲና ቤሩት ውስጥ በነበረው የዛሬው ንግግር የቆጵሮስ ፕሬዚደንት ኒኮስ ክርስቶዶሊዱስም እንደነበሩበት ተዘግቧል ። ከንግግሩም በኋላ የአውሮጳ ኅብረት ለሊባኖስ የ1,07 ቢሊዮን ዶላር ድጋፉ እንደሚሰጥ ይፋ ተደርጓል ። ለመሆኑ የአሁኑ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ያስፈለገበት ምክንያቱ ምንድን ነው?
የአውሮጳ ኅብረት ስደተኞች ወደ ግዛቱ እንዳይመጡበት ለማከላከል መሰል ስምምነቶችን ቀደም ሲልም እንደ ቱርክ፤ ግብጽ፤ ሞሮኮ፤ ሊቢያ እና ቱኒዝያ ከመሳሰሉ ከተለያዩ ሃገራት ጋርም ማድረጉ የሚታወስ ነው ። ኅብረቱ በሚፈልገው መጠን ስደተኞችን በዚህ መቆጣጠር ችሏል?
ጦርነት በብርቱ ያዳቀቃት ሶሪያ ስደተኞች በሊባኖስ በኩል 160 ኪሎ ሜትር በጀልቦች በመቅዘፍ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገር ወደ ሆነችው ቆጵሮስ በየቀኑ ይፈልሳሉ ። ባለፉት አራት ወራት ብቻም በዚህ መልኩ ወደ 4,000 የሚጠጉ የሶርያ ስደተኞች ቆጵሮስ መግባታቸው ተዘግቧል ።
ስደተኞች ከየሃገሮቻቸው በተለያዩ ምክንያቶች መፍለሳቸው ይታወቃል ። በዋናነት ግን የዴሞክራሲ እጦት፤ አምባገነንነት እና ጦርነት ለፍልሰት ሰበብ መሆናቸው በተደጋጋሚ ይነገራል። የአውሮጳ ኅብረት የተጠቀሱት የስደት ሰበቦች እንዳይኖሩ አለያልም እንዲቀንሱ ማድረጉ ላይ ለምንድን ነው ያልበረታው ወይንም ያልተሳካለት?
ሙሉ ቃለ መጠይቁን ከድምፁ ማእቀፍ ማድመጥ ይቻላል
ገበያው ንጉሤ/ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ