1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲስ አበባ ሰባራ ባቡር አከባቢ ልማት ተነሺዎች ቅሬታ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 15 2017

«እኛ ያልመረጥነው ጊዜያዊ ነው በማለት አያት አከባቢ ኮንዶሚኒየም እንድንገባ ግድ ነው አሉን፡፡ ልጆች አሉን፡፡ ነፍሰጡርና አራስ ሴቶች አሉን፡፡»

https://p.dw.com/p/4oY4Q
“ለኑሮ የሚሆን መሰረታዊ ነገር ሳይሟላልን መነሳታችን ተገቢ አይደለም”
“ለኑሮ የሚሆን መሰረታዊ ነገር ሳይሟላልን መነሳታችን ተገቢ አይደለም”ምስል Seyoum Getu/DW

«የሰሚ ያለህ»

የአዲስ አበባ ሰባራ ባቡር አከባቢ ልማት ተነሺዎች ቅሬታ
አዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 በተለምዶ ሰባራ ባቡር ተብሎ ከሚጠራው አከባቢ ቦታው ለልማት ይፈለጋል በሚል እንዲነሱ የተጠየቁት ነዋሪዎች እንድንዘዋወር ግፊት እየቀረበብን ያለው ለኑሮ ያልተመቻቸ መሰረታዊ ነገር በሌሌበት ተለዋጭ ቤቶች ነው ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ፡፡
ለዘመናት በዚያው ስንኖር እስከ ሶስት ትውልድ ዘልቀናል ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ አሁን ላይ ቦታው ለባለሀብቶች በመሸጡ 72 አባወራዎች ምንም መሰረታዊ አገልግሎቶች ባልተጠናቀቀበት ወደ አያት እንድትነሱ ተብለናል ነው የሚሉት፡፡
ነዋሪዎቹ ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ጉዳያቸውን በቅርበት በማየት እልባት እንዲሰጡዋቸውም ተማጽነዋል፡፡

የቅሬታ አቅራቢዎቹ ጭብጥ
ቅሬታቸውን ከገለጹት 72 አባወራ ነን ያሉ የአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ነዋሪዎቹ አስተያየት ሰጪዎች አንደኛዋ “እኛ የምንኖረው ሰባራ ባቡር አረቄ ፋብሪካ ጀርባ ነው፡፡ ቶታል ማደያ ጎን ማለት ነው፡፡ እስከ አሁን እኛ ያለንበት አያታችን የኖሩበት ነው፡፡ አሁን ባለሃብት ቦታውን ገዝቷል ተብለን ነው እንድንነሳ የሆነው፡፡ ከዚያ  ምን ትመርጣላችሁ አሉን፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤት ወይስ የቀበሌ ቤት ሳሲሉን የቀበለ ቤት እንመርጣለን አልን፡፡ በዚሁ እያለን ኑ እቃ አውጡ አሉን፡፡ ከዚህ እኛ ያልመረጥነው ጊዜያዊ ነው በማለት አያት አከባቢ ኮንዶሚኒየም እንድንገባ ግድ ነው አሉን፡፡ ልጆች አሉን፡፡ ነፍሰጡርና አራስ ሴቶች አሉን፡፡ ሰባት ቤተሰብ ያለው ሁሉ አለ፡፡ ህንጻውን ስንመለከተው ግን ቤቶቹን ሸንሽነውት ለወንደላጤ እንኳ የሚበቃ አይደለም፡፡ ያ ራሱ ቢሆን እዛ ሄደን ልጅ እንኳ ታሞብህ የምታሳክምበት የለም፡፡ ይባስኑ እቃችሁን  እንጭንላችኋለን ያሉን አሁን ደግሞ በራሳችሁ ጫኑ አሉን” ሲሉ አማረዋል፡፡

««ያልተሟላውን ግንባታ እንኳ ገብተንበት እንዳንጨርስ መንካት አትችሉም ዝም ብላችሁ ቀለም ቀብታችሁ ብቻ መኖር ነው የምትችሉ አሉን፡፡»
«ያልተሟላውን ግንባታ እንኳ ገብተንበት እንዳንጨርስ መንካት አትችሉም ዝም ብላችሁ ቀለም ቀብታችሁ ብቻ መኖር ነው የምትችሉ አሉን፡፡»ምስል Seyoum Getu/DW


የተዘጋጀው አዲስ ስፍራ የመሰረተ ልማት መጓደል
ሌላም ነዋሪ አስተያየታቸውን አከሉ፤ “ከመጀመሪያው ጀምሮ አወሊያ ትምህርት ቤት ቦታውን መርጦታል ተባልን፡፡ እሺ ብለን ተስማማን፡፡ ተነሺዎች 72 አባወራዎች ናቸው፡፡ 52 አባወራዎች ተመርጠው አያት አከባቢ ተዘጋጀ ወደ ተባለው 40/60 የጋራ መኖሪያ ወስደው አሳዩን፡፡ ቦታውን ሄደን ካየን በኃላ እዚህ ግባ የምትባል አይደለችም፡፡ አንድ ቤት ስድስት ሰባት እስከ 13 ሆኖ የሚኖር አለ፡፡ መጀመሪያ ስብሰባው ላይ የተባልነው እቃ ጫኝ ተሸከርካሪ ተዘጋጅቶላችኋል የምትሄዱበት ቦታ ከዚህ የበለጠ ነው ተብለን ነበር፡፡ ዛሬ ግን መጥተው እቃችሁን በራሻችሁ ብር ወስዳችሁ አስጭኑ አሉን፡፡ ከኛ ግን ያን እንኳ የማድረግ አቅም ያለው አንድም ሰው የለም፡፡ ባለሃብት ካነሳህ መቼም ሳይከፍል አሆንምና እኛም ምቾት ተሰምቶን ብንነሳ ነበር መልካም የሚሆነው” ብለዋል፡፡
ሌላም ቅሬታ አቅራቢ አስተያየታቸው ቀጠሉ “የተሰጠን ነገር በአግባቡ አይደለም፡፡ አሁን ጊዜያዊ ነው በሚል ከአንደኛ እና ሁለተኛ ወለል የተጠተን ለቢዝነስ የተባለውን ቤት ሸንሽነው ነው፡፡ ሽንትቤትና ማብሰያ የሌለው ቤት አለ፡፡ ሰፊው 25 ካሬ ነው፡፡ መብራትና ውሃ ገና ይገባላችኋል ተብለናል፡፡ ያልተሟላውን ግንባታ እንኳ ገብተንበት እንዳንጨርስ መንካት አትችሉም ዝም ብላችሁ ቀለም ቀብታችሁ ብቻ መኖር ነው የምትችሉ አሉን፡፡ የፈሳሽ መተላለፊያ እንኳ ያልተገጠመለት ቤት አለ፡፡ በዚያ ላይ ታማሚዎች አሉን፡፡ ያም ሆኖ እስከ እሮብ ታህሳስ 16 ተስተካከሉ ነው የተባልነው” ብለዋል፡፡


ጉዳያቸው በከተማ አስተዳደሩ እንዲታይላቸው ያሰሙት ተማጽእኖ
“ለኑሮ የሚሆን መሰረታዊ ነገር ሳይሟላልን መነሳታችን ተገቢ አይደለም” የሚሉት ነዋሪዎቹ የከተማአስተዳደሩ ችግሮቻቸውን በቅርበት እንዲመለከትላቸውም ተማጽነዋል፡፡ “እንደ ሌላው አከባቢ ተነሺዎች የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጉዳያችንን ይመልከቱልን” ሲሉም የልማት ተነሺ ነዋሪዎቹ አቤት ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተለያዩ አከባቢዎች ከዚህ በፊት ለልማት ያነሷቸውን ነዋሪዎች በተሻለ መሰረተ ልማት መልሶ እንዳቋቋማቸው በተደጋጋሚ ስገልጽ ተደምጧል፡፡ አሁን ከሰባራ ባቡር አከባቢ ልነሱ ነው የተባሉት የልማት ተነሺዎች ስላቀረቡት ቅሬታ ዶቼ ቬለ ተጨማሪ አስተያየት ለማግኘት ለከተማ አስተዳደሩ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ እናታለም መለሰ፣ ለከተማ አስተዳደሩ ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ የንጋት ኮከብ እና ለአራዳ ክፍለ ከተማ 02 ወረዳ የቤቶች ልማት ኃላፊ አቶ ጌታሁን በተደጋገሚ የስልክ ጥሪና መልእክት በመላክ ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡
ሥዩም ጌቱ 
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ