„ሄር ሂሴ“ ዩኔስኮ እውቅና የሰጠው የሂሳ ማህበረሰብ ያልተፃፈ ባህላዊ ሕግ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 17 2017ከሳምንታት በፊት በፓራጓይ 19 ኛ ዓመታዊ ጉባዔውን ያካሄደው አለም አቀፉ የትምህርት ፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በእንግሊዘኛ ምህፃሩ - UNESCO ኢትዮጵያ ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ በጋራ ላቀረቡት የሂሳ ማህበረሰብ ሀብት የሆነው ቅርስ ይመዝገብልን ጥያቄ አዎንታዊ ውሳኔ ሰጥቷል። በመድረኩ በሦስቱ ሀገራት የሚኖረው የሶማሌ ሂሳ ማህበረሰብ ሀብት የሆነው ያልተፃፈው ባህላዊ ህግ - ሄር ሂሴ በሰው ልጆች የማይዳሰስ ወካይ ቅርስነት እንዲመዘገብ ያደረገው ውሳኔ በየሀገራቱ የሚኖረውን የሂሳ ማህበረሰብ በእጅጉ አስደስቷል። በሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ወደ ሀገር ሲመለስ የማህበረሰቡ መሪ የሆኑት ዑጋዝ መቀመጫ በሆነችው ድሬደዋ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለት ቅርሱ እውቅና አግኝቶ የተመዘገበበትን ሰርተፍኬት ለዑጋዙ አስረክበዋል። መሰል የደስታ መግለጫ መድረክ በጅቡቲ ሲካሄድ በሶማሊያ ቀጠሮ ተይዞለታል።
"ሄር ሂሴ" - የሶማሌ ዒሳ ማህበረሰብ ባህል በዩኔስኮ ተመዘገበ
አቶ ደበበ ዘውዴ በ2001 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሁለተኛ ዲግሪ ማሟያነት በሂድ ማህበረሰብ ያልተፃፈ ሕግ - ሄር ሂሴ ላይ ጥናት ያካሄዱ ባለሞያ ናቸው። ሕጉን በሚመለከት ለዶይቼ ቬለ አስተያየት የሰጡት ባለሞያው፣ ሄር ሂሴ በምስራቅ አፍሪካ የሚኖሩ የማህበረሰቡ አባላት የሚዳኙበት ነው ይላሉ። ባህላዊ እና አስተዳደራዊ ገፅታ እንዳለው ያነሱት አቶ ደበበ ይዘቶቹንም አብራርተዋል።
የሕጉ ሁለተኛ አካል የማህበረሰቡ መሪ የሆነውን የዑጋዝ አመራረጥ ፣ ባህላዊ አስተዳደር እና ባህላዊ ዳኝነትን የተመለከቱ አወቃቀሮች እንዳሉት ባለሞያው አስረድተዋል።የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው ግጭቶችን ለመፍታትና ለመከላከል የወጣ ሕግ ነው ያሉት ሄር ሂሴ ተመሳሳይ እጣ ፈንታ አላቸው ያሏቸውን የአካባቢው ማህበረሰብ አንድነት ይበልጥ እንዲያጠናክሩ የሚያግዝ መሆኑን ለዶይቼቬለ ተናግረዋል።
የሸዋል ኢድ በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ ሀረሪዎችን አስደስቷል
ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረውን እና የሶማሌ ህዝብ አካል የሆነውን የሂሳ ማህበረሰብ መተዳደርያ ሕግ እውቅና እንዲያገኝ ከአምስት አመታት በላይ ያስቆጠሩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።
ከአምስት አመት በፊት የተመሰረተው ሲቲ ሄሪቴጅ - ከትውልድ ትውልድ ተሸጋግሮ እዚህ የደረሰውን ሄር ሂሴን በአለም ዓቀፉ የትምህርት ፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም እውቅና እንዲያገኝ የሚያስችሉ ስራዎች ለመስራት የተቋቋመ ማህበር ነው። በእውቅናው መርሀ ግብሩ ማግስት የማህበሩ ኃላፊ ወ/ሮ አያን አብዲ ለውጤቱ ብዙ ስራዎች መስራታቸውን አብራርተዋል። በውጤቱም መደሰታቸውን በመግለፅ። ሄር ሂሴ በዩኔስኮ በሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ በማህበረሰቡ አባላት ዘንድ ትልቅ ደስታን ፈጥሯል።
የተገኘውን እውቅና አስመልክቶ ለዶይቼ ቬለ ስሜታቸውን ያጋሩት የዑጋዛዊው ምክር ቤት ቃል አቀባይ አቶ መሀመድ ሙሴ ጌሌ ተከታዩን ብለዋል። ያልተፃፈው የሂሳ ማህበረሰብ ባህላዊ ሕግ ሄር ሂሴ ተጠብቆ ለእውቅና እንዲበቃ የማህበረሰቡ ጥንካሬ አስተዋፅኦው ትልቅ መሆኑን በሕጉ ላይ ጥናት ያካሄዱት አቶ ደበበ ጠቁመዋል። የዘመናት እድሜን ያስቆጠረው ሄር ሂሴ አሁን አለም አቀፍ ቅርስ ሆኗል።
ዩኔስኮ ለመዘገባቸዉ የኢትዮጵያ ቅርሶች ጥበቃ ያደርጋል?
ባህላዊ ህጉ አለም አቀፉን እውቅና ማግኘት ተከትሎ በወጣቶች ዘንድ መነቃቃት መፈጠሩን ያነሱት ቶ ኢብራሂም መመዝገቡ የተለያየ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል።
የዑጋዝ ምክር ቤት ቃል አቀባይ አቶ መሀመድም እውቅናው ብዙ ጠቀሜታ አለው የሚል እምነት አላቸው።
ከሳምንታት በፊት በፓሯጋይ በተካሄደ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ የሰው ልጆች የማይዳሰስ ወካይ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው ሄር ሂሴ ሀገራዊና እና አለምአቀፋዊ ፋይዳዎች እንዳሉት ያነሱት በህጉ ላይ ጥናት ያካሄዱት አቶ ደበበ ሀገራዊ ያሏቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል። በሌላ በኩል የማህበረሰቡ መኖርያ የሆኑትን ኢትዮጵያ ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያን ያስተሳሰረ መሆኑን በማንሳት አለም አቀፋዊ ፋይዳውንም አብራርተዋልል።
መሳይ ተክሉ
ኂሩት መለሰ