1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩኔስኮ ለመዘገባቸዉ የኢትዮጵያ ቅርሶች ጥበቃ ያደርጋል?

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 11 2016

«ላሊበላ በጦርነቱ አደጋ ደርሶበታል የሚለዉ ጉዳይ አንደኛ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ሁኔታዉን ቦታዉ ላይ የሚከታተል ሰዉ አለዉ። እኛም ሄደን አይተናል። ላሊበላን እንደ ዓይናችን ብሌን እንጠብቀዋለን። ስለዚህ ይህ በቤተ-ክርስትያኑ አደጋ ደረሰ የተባለዉ ነገር ቀና አስተሳሰብ የሌላቸዉ ሰዎች የሚያሰራጩት የሃሰት ዘገባ ነዉ።» የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን

https://p.dw.com/p/4aRjz
ዩኔስኮ ስብሰባ፤ የኢትዮጵያ መልዕክተኞች
ዩኔስኮ ስብሰባ፤ የኢትዮጵያ መልዕክተኞችምስል Permanent Delegation of Ethiopia to UNESCO

በጦርነት ግጭት ዉስጥ የሚገኙ ቅርሶች በጦርነት እንዳይጎዱ ምን አይነት ከለላ ይደረግላቸዋል?

«በአፍሪቃ ደረጃ ስንሄድ፤ የተባበሩት መንግሥታት፤ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አባል ስንሆን የመጀመርያ ነን» ይህን ያሉት ፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ናቸዉ።

ከቅርብ ሳምንታት በፊት በሐረሪዎች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል፤ የሸዋል ኢድ በዓል አከባበርን፤ በተባበሩት መንግሥታት፤ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ አድርጎ መዝግቧል። ከዚህ ቀደም ሲል መስከረም ወር ላይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር እና በኦሮሚያ ክልል የሚገኙት የባሌ ተራሮች፣ የዓለም ቅርስ ሆነው መመዝገባቸዉ ይታወቃል። ኢትዮጵያ በዓለሙ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን 16 የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ተፈጥሮዋዊና ባህላዊ ቅርሶችን አስመዝግባለች። ግን የዓለሙ የቅርስ ጥበቃ ድርጅት በየሃገሩ የመዘገባቸዉን ቅርሶች ጥበቃ እና ከለላ የሚሰጠዉ እንዴት ነዉ? በጦርነት ግጭት ዉስጥ የሚገኙ ቅርሶች በጦርነት እንዳይጎዱ ምን አይነት ከለላ ይደረግላቸዋል? የሸዋል ኢድ በዓል አከባበር በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ኢትዮጵያዉያን ደስ ሊለን ይገባል እንኳን ደስ ያለን ስል ቃለ ምልልስ የጀመርኩላቸዉ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌውን ነዉ። ዋና ዳይሬክተሩ፤  አዎ ደስ ብሎናል ብለዋል። ቦትስዋና ካሳኔ ከተማ የተካሄደዉ የዩኔስኮ ስብሰባ

የተመዘገቡ የኢትዮጵያ ቅርሶች

«ቦትስዋና ካሳኔ ከተማ በተካሄደዉ የዩኔስኮ ስብሰባ ፤ ሸዋል ኢድ የሚባለዉን እና በሀረር ከተማ በሀረሪ ህዝቦች ዘንድ የሚከበረዉ በዓል፤ ከረመዳን በኋላ ከስድስት ቀን ፆም በኃላ ስድስተኛዉ ቀን ምሽት ላይ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚከበረዉ በዓል ነዉ በማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ የተመዘገበዉ። የሀረሪን ህዝብ ብሎም የኢትዮጵያን ህዝብ እንኳን ደስ ያላችሁ እንኳን ደስ ያለን ማለት እፈልጋለሁ።

ቦትስዋና ካሳኔ ከተማ የተካሄደዉ የዩኔስኮ ስብሰባ
ቦትስዋና ካሳኔ ከተማ የተካሄደዉ የዩኔስኮ ስብሰባምስል Permanent Delegation of Ethiopia to UNESCO

በአፍሪቃ ቅርሶችን በማስመዝገብ ቀዳሚዋ ሃገር ሆናለች፤ ደስ ሊለን ይገባል ሲሉ የነገሩን በፈረንሳይ ፓሪስ የኢትዮጵያ ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሳይንስ፣ የትምህርት እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ምክትል ቋሚ መልእክተኛ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ናቸዉ።

«ኢትዮጵያ በአፍሪቃ በዩኔስኮ በማስመዝገብ ቀዳሚዉን ስፍራ ይዛለች። በጎርጎረሳዉያኑ 1972 ዓም የዓለም ስምምነት ከፀደቀ ከ 51 ዓመታት በኋላ ሃገራችን ኢትዮጵያ 11 የሚዳሰሱ ቅርሶችን አስመዝጋባለች። አፍሪቃ በ 50 ዓመታት ዉስጥ 101 ቅርሶችን ነዉ ያስመዘገበዉ ከዝያ ዉስጥ 11 ዱ ቅርሶች የኢትዮጵያ ናቸዉ። በዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ዉስጥ የባህልና የተፈጥሮ ቅርሶችን በማስመዝገብ ቀዳሚዋ ሃገር አድርጓታል። በአፍሪቃ ዉስጥ እስካሁን ድረስ 12 የሚሆኑ ሃገራት አንድም ቅርስ ማስመዝገብ አልቻሉም።

«የዓለም ቅርስ ናቸዉ ሲባል አንደኛ ለእንክብካቤ የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ሁለተኛ ክትትል ይደረግባቸዋል። ሦስተኛ የቱሪስትን ፍሰት ይጨምራል። እንደሚታወቀዉ በዩኔስኮ የተመዘገበ ቅርስ ያላቸዉን ሃገራት ነዉ ቱሪዝሙ ተከትሎ የሚሄደዉ። ሃብትም ለማፍራት ይህንኑ ተከትሎ ነዉ የሚጓዘዉ። ሌላዉ በነዚህ ቅርሶች ላይ አንድ አደጋ ከተከሰተ የቅርሱ ባለቤት ሃገር ብቻ ሳይሆን የዓለም ማኅበረሰብ ጭምርም ነዉ። ለምሳሌ የአስዋን ግድብ ሲገነባ ፤ አካባቢዉ ላይ የነበረዉን ቅርስ በመጉዳቱ የዓለም ማኅበረሰብ ተረባርቦ ቅርሱን ለማደስ በቅቷል። ሌላዉ ምሳሌ በፈረንሳይ ፓሪስ ሮተርዳም የተባለዉ ካቴድራል በእሳት ሲጋይ 24 ሰዓታት ባልሞላ ጊዜ ነዉ የዓለም ህዝብ ወደ 800 ሚሊዮን ዶላር ያሰባሰበዉ። በቅርስ ላይ ለሚከሰት ማንኛዉም ችግር፤ ቀዳሚዉን ኃላፊነት የሚወስደዉ የሃገሪቱ መንግሥት ቢሆንም፤ የዓለሙ የቅርስ ጥበቃ ድርጅት ከፍተና ሃላፊነትን ወስዶ ክትትል ያደርጋል ፤ያድሳል። » ሲሉ ግን ዶ/ር ጥላዬ በቅርስነት ተመዘገበ ማለት ለቅርሶቹ የዓለሙ ድርጅት ከለላ መስጠቱን አስረድተዋል።

ላሊበላ ዉቅር አብያተ ክርስትያን
ላሊበላ ዉቅር አብያተ ክርስትያንምስል Solan Kolli/AFP/Getty Images

ስለ ላሊበላ አብያተ ክርስትያናት አደጋ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምን ይላል?

በቅርቡ በሰሜን ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በሚካሄደዉ ጦርነት በላሊበላ ከተማ የሚገኘዉ የላሊበላ አብያተ ክርስትያናት ላይ የመናጋት ጉዳት ደርሷል የሚል ዘገባ ሰምተናል፤ የአካባቢዉ ማኅበረሰብም ሲናገሩ ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ የተነገረ ነገር አለ?

«አዎ በላሊበላ ብቻ ሳይሆን፤ ከሁለት ዓመት በፊት በትግራይ ክልል በነበረዉ ጦርነት ሳብያ ችግሮች በአክሱም ሃዉልት ላይ እንዲሁም በጎንደር ጥንታዊ ቤተ መንግሥት ላይ አደጋ አጋጥሟል የሚል ነገር ተነስቶ፤ ዩኔስኮ ከአካባቢዉ ላይ የሚደርሰዉን ጥቆማ ይዞ፤ ማብራርያ ይጠይቃል። ጠይቆናል ማብራርያ ሰጥተናልም። በላሊበላ ዉቅር አብያተ ክርስትያን ላይ ደረሰ ለተባለዉ አደጋ ፤ ትክክል ናቸዉ አይደሉም የሚለዉን ፤ ምንድን ነዉ መደረግ ያለበት የሚለዉን የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ረዳት ፕሮፌሰር አበባዉ አያሌዉ፤ ተገቢዉን መግለጫ ሰጥተዋል። በጽሑፍም ለዩኔስኮ የባህል ማዕከል ሰጥተዋል። እኔም ከአገራችን ያገኘነዉን መረጃ ይዤ ለዩኔስኮ የአፍሪቃ ባህል ማዕከል ዳይሬክተር በቅርሱ ላይ ምንም አይነት የከፋ ችግር እንዳልደረሰ እና ይህንንም የኢትዮጵያ መንግሥት ተገቢዉን ክትትል እያደረገ መሆኑን ተገቢዉን ማብራርያ ሰጥተናል።»  

የተባበሩት መንግሥታት፤ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ)
የተባበሩት መንግሥታት፤ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ)ምስል Alain Jocard/AFP/dpa/picture alliance

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እዚህ ላይ አንድ ቅርስ በዩኔስኮ ተመዘገበ፤ ጥበቃ ይደረግለታል ማለትስ ምን ማለት ነዉ?

«አንድ ሃገር ይህ ቅርሴ በተባበሩት መንግሥታት፤ የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ይመዝገብልን ብሎ ሲሰጥ እና ሲመዘገብ፤ ይህ ቅርስ የኔ ብቻ ሳይሆን የዓለም ነዉ ብሎ ጥበቃ እንዲደረግለት ነዉ»

ይህ ጥሩ ነዉ፤ ይሁንና በሰሜን ኢትዮጵያዉ ጦርነት  ቅርሶች እንደወደሙ ተዘግቧል፤ አሁን በቅርቡ በአማራ ክልል በሚደረገዉ ጦርነት በተለይ በላሊበላ አብያተ ክርስትያናት ላይ ከፍተኛ አደጋ መጋረጡን የአካባቢዉ ነዋሪዎች ሲናገሩ ተሰምቷል ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ዩኔስኮ ያነሳዉ ነገር አለ ፤ የሚያደርገዉርገዉስ ርምጃ አለ ተቋሙ?

«ላሊበላ ትልቅ ቅርስ ነዉ በዓለም ላይ ይህን መሰል ቅርስ የለም። ለቅርሱ ጥበቃ የፈረንሳይ መንግሥት እየረዳ ነዉ። ከዚህ ቀደምም የአዉሮጳ ህብረት ለዉቅር አብያተክርስትያኑ መጠለያ ገንብቷል። መጠለያዉ ከፀሐይም ከዝናብም እንዲከላከል ነዉ። ይሁንና አሁን ደግሞ መጠለያዉን እንደገና ለማበጀት የፈረንሳይ መንግሥት ጥናት እያደረገ ነዉ ይሁንና በኮሮና ወረርሽኝ እና አካባቢዉ ላይ ባለዉ ግጭት ምክንያት እስካሁን እንደታሰበዉ ስራዉ ተፋጥኖ አልተሰራም። ይሁንና አሁን በጦርነቱ አደጋ ደርሶበታል የሚለዉን ጉዳይ በሁለት መንገድ ነዉ ማስረዳት የምፈልገዉ። አንደኛ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የሚከፍለዉና ሁኔታዉን እዛዉ ቦታ ላይ የሚከታተል ስላለ በየቀኑ ስለሁኔታዉ ዘገባ ይደርሰናል። ሁልጊዜም ላሊበላን እንደ ዓይናችን ብሌን በደንብ አድርገን ነዉ የምንከታተለዉ እና የምንጠብቀዉ። ስለዚህ ይህ በላሊበላ ዉቅር አብያተ ክርስትያን ላይ አደጋ ደረሰ የተባለዉ ነገር ቀና አስተሳሰብ የሌላቸዉ ሰዎች የሚያሰራጩት ዘገባ ነዉ። »

ሸዋል ኢድ ክብረ በዓል በሀረር

የሸዋል ኢድ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሀረር መከበር እንደተጀመረ የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ። ይህ ክብረ በዓል በሐረሪ ሕዝባዊ እና ባህላዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር ጥቅምት 8 ቀን 1999 ዓ.ም በአዋጅ በመደንገጉ በአካባቢዉ ላይ በድምቀት የሚከበር በዓል ሆኖ ቀጥሏል። ይህ ክብረ በዓል ቀደም ባሉት ዓመታቶች፤ ከሃረሪ ወጣ ብሎ በሃገሪቱ ደምቆ ያልወጣና እምብዛም የማይታወቅ ነበር።  የሸዋል ኢድ አከባበር በዓለሙ መዝገብ በማይዳሰስ ቅርስ ሲመዘገብ፤ ምን አስተያየቶች ተሰጠዉ ይሆን? የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) ኢትዮጵያ እንደመታደል ሆኖ በአራት ነገሮች መነሳትዋን ይገልፃሉ።    

የሸዋል ኢድ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሀረር መከበር ጀመረ
የሸዋል ኢድ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሀረር መከበር ጀመረ ምስል Mesay Tekelu/DW

«ኢትዮጵያ እንደመታደል ሆኖ በአራት ነገር ትነሳለች። ሀገሪቱ የክርስትና የእስልምና የይሁዲ እምነት በተጨማሪ  ግሪኮችም ኢትዮጵያን እንደትልቅ ሀገር ነዉ የሚያነስዋት። እስልምና ከኢትዮጵያ ጋር ያለዉ ቁርኝት በጣም የጠበቀ ነዉ። በተለይ ምስራቅ ኢትዮጵያን ስንወስድ ሀረር የተለየች ናት። ሀረር ከተማ በምስራቅ አፍሪቃ ቀደምት እና ትልቁ የእስልምና ትምህርት ማዕከል የነበረች ናት። በንግድም ረገድ ብንወስድ ሀረር በጣም ትልቅ እና የራስዋ የመገበያያ ሳንቲም የነበራት ታዋቂ የንግድ ማዕከል ነበረች። ከዚህ በተጨማሪ ሀረር የጀጎል ግንብ እና የከተማዋን የሥነ-ህንጻ ዘዴን ባለፈዉ በጎርጎረሳዉያኑ 2006 በቅርስነት አስመዝግባለች። ግን ሃረር የማይዳሰስ ቅርስም ብዙ አላት። አሁን የሸዋል ዒድ ክብረ በዓል በማይደሰስ ቅርስነት ተመዝግቧል።»

ቀጣይ የሚመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን፤ በጎርጎረሳዉያኑ 2024 የመልካ ቁንጡሬ መካነ ቅርስና፤ የኢሳ ባህላዊና አፋዊ የህግ  ስርዓትን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በሂደት ላይ መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው ተናግረዋል። የኢሳ ባህላዊና አፋዊ የህግ ስርዓትበኢትዮጵያ፣ በሶማሊያና በጁቡቲ መካከል የሚከናወን በመሆኑ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ በአፍሪቃ ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ በሦስት ሃገራት ዘንድ የሚመዘገብ የመጀመሪያ ቅርስ እንደሚሆንም አበባዉ አያሌዉ ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ካላት ልምድ በመነሳትም ሥራዉን በባለቤትነት እየሰራች መሆኑን ነዉ የነገሩን።

ቦትስዋና ካሳኔ ከተማ የተካሄደዉ የዩኔስኮ ስብሰባ፤ የኢትዮጵያ መልዕክተኞች
ቦትስዋና ካሳኔ ከተማ የተካሄደዉ የዩኔስኮ ስብሰባ፤ የኢትዮጵያ መልዕክተኞችምስል Permanent Delegation of Ethiopia to UNESCO

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን የኢትዮጵያ ባህላዊ ሃብት ለዓለም እያስተዋወቀ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነዉ። ባለሥልጣን መስርያ ቤቱ እንደገለፀዉ በጥበቃዉም ረገድ የተመዘገቡ ቅርሶችን በተመለከተ በየእለቱ ክትትል በማድረግ መቆጣጠሩን ያነጋገርናቸዉ የባለሥልጣን መስርያ ቤቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ነግረዉናል። የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እና በፈረንሳይ ፓሪስ የኢትዮጵያ የዩኔስኮ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።  

አዜብ ታደሰ   

እሸቴ በቀለ